በሰሜን ሸዋ ዞን 82 ቀበሌዎችን እርስ በእርስና ከዋና የሚያገናኙ መንገዶች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

150
ደብረ ብርሃን ሀምሌ 30/2010 በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገዶች ፕሮግራም የተሰሩ መንገዶች ያሉባቸውን ክፍተት በመሙላት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን የሰሜን ሽዋ ዞን መንገድና ትራንስፖርት ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የፕሮጀክት ኮንትራክት አስተዳደር ቡድን ሱፐርቫይዘር መሀንዲስ አቶ ሞገስ ዜና እንደገለጹት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በ16 ወረዳዎች በፕሮግራሙ አንድ ሺህ 383 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገዶች  ተሰርተዋል፡፡ የተሰሩ መንገዶችም 82 ቀበሌዎችን እርስ በእርስና ከዋና መንገዶች ጋር በማገናኘት 310 ሺህ 370 ሰዎች ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጅ “በመንገዶች ላይ የውሃ ማፋሰሻ ቦይ፣ ዲች፣ የቱቦ ቀበራና የአነስተኛና መለስተኛ ድልድዮች እንዲሁም ሌሎች ስትራክቸሮች ባለመሰራተቸው በተለይም በክረምት ወቅት ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጡ ቆይተዋል'' ብለዋል፡፡ በክልሉ መስተዳድር በተመደበ 32 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት ስትራክቸሮችን በመስራት መንገዶቹ ክረምት ከበጋ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከተመደበው በጀት ውስጥ 18 ሚሊዮን 728 ሺ ብር በባሶና ወራና፣ በአንኮበርና በምንጃር ሸንኮራ ወረዳዎች ከ200 በላይ ስትራክቸሮችን በመገንባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በአንጸሩ ኤፍራታና ግድም፣ በረኸት፣ መራቤቴ፣ ጣርማበርና መንዝ ላሎ ወረዳዎች አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ተገምግሞ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል። በአንኮበር ወረዳ የመሃል ወንዝ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ግርማ ሀብተማሪያም በሰጡት አስተያየት በ2007 ዓ.ም  ቀበሌያቸውን ከአጎራባች ቀበሌዎችና ዋናው መንገድ የሚያገናኝ 10 ኪሎ ሜትር ጠጠር መንገድ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡ ቱቦ፣ ጎርፍ ተፋሰስና ቀላል ድልድይ ባለመሰራቱ ምክንያት መንገዱ ለተሽከርካሪ ክፍት ባለመሆኑ ለመኸር እርሻ ግብዓቶችን ለማስገባትና ወላድ እናቶችንና የግብርና ምርታቸውን ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ ሲቸገሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ዘንድሮ በክረምቱ መግቢያ አካባቢ በመንገዱ ላይ የተጓደሉ ስራዎች በመገንባታቸው መኪና በመንደራቸው ጧትና ማታ በማለፉ የነበረባቸው ችግር መቀረፉን ተናግረዋል፡፡ በባሶና ወረና ወረዳ የበደሌ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አባትነህ ተስፋዬ ቀበሌያቸውን ከአንኮበር ዋና መንገድ በሚያገኘቸው መንገድ ላይ የቱቦ፣ የጎርፍ ማፋሰሻና ሌሎችም ጥቃቅን ነገሮች በመገንበታቸው በክረምት ይቋረጥ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት አሁን ላይ መቀጠሉን ተናግረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም