የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2014 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀትን በሙሉ ድምጽ አጸደቀ

65

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2013(ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2014 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀትን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አራተኛ ልዩ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ አካሄዷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው 97ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2014 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 561 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ውሳኔ በማሳለፍ በጀቱ እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ የሚታወስ ነው።

ምክር ቤቱም የቀረበውን የ2014  በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፤በጀቱ አዋጅ ቁጥር 1254/2013 በሚል ነው የጸደቀው።

የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት ለመደበኛ ወጪዎች ብር 162 ቢሊዮን፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 183.5 ቢሊዮን፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 203 ነጥብ 95 ቢሊዮን፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 12 ቢሊዮን ተመድቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም