በአዊ ዞን ከመስኖ ልማት ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኘ

56
ባህር ዳር ሀምሌ30/2010 በአዊ ዞን ባለፈው የበጋ ወራት የከርሰና ገፀ ምድር ውሃን በመጠቀም በመስኖ ከለማው መሬት ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመስኖ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮችም የተሻለ ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ አዲሱ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ምርቱ የተሰበሰበው በአንደኛና ሁለተኛ ዙር መስኖ ከለማው 88 ሺህ 320 ሄክታር መሬት ነው። በመስኖ ልማቱ የተሳተፉ ከ142 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮችም ፈጥነው የሚደርሱ የገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ድንች፣ የጓሮ አትክልት፣ ቅመማቅመምና ሌሎች ሰብሎችን በማልማት ተጠቃሚ ሆነዋል። ለመስኖ ልማቱም ከ97 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር፣ እንዲሁም 218 ሺህ ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል። ባለፈው የበጋ ወራት በመስኖ የለማው መሬት ከቀዳሚው ዓመት በ14 ሺህ 292 ሄክታር፣ በምርት ደግሞ በ794 ሺህ ኩንታል መቀነሱን አስረድተዋል። የቀነሰበት ምክንያት በዞኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርሶአደሩ የተሻለ ገቢ አገኝበታለሁ ብሎ ባመነበት የደን ችግኝ የመስኖ መሬትን እየሸፈነ በመምጣቱ ነው። በዞኑ ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የአጉታወጀላ ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃኑ አየን በመስኖ ልማት መጠቀም ከጀመሩ 10 ዓመት እንደሆናቸው ተናግረዋል። “በበጋ ወራት በአንድ ከሩብ  ሄክታር መሬት በመስኖ የአፕል ችግኝ ከማዘጋጀት ጀምሮ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ገብስ፣ ድንችና ሌሎች ሰብሎችን በማልማት ተጠቃሚ እየሆንኩ ነው” ብለዋል። በአንድ የበጋ ወራት ግማሽ ሄክታር መሬት እስከ ሁለት ጊዜ በተለያዩ የጓሮ አትክልትና ሌሎች ሰብሎች በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፈቃዱ ቢተውልኝ ናቸው። አልምተው ከሚያገኙት ምርት ከራሳቸው ፍጆታ የተረፋቸውን ለገበያ በማቅረብም በየዓመቱ እስከ 7 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል። በክረምት ወቅት ዝናብን ጠብቀው አልምተው ከሚሰበስቡት ያልተናነሰ ምርት በበጋ ወቅት ከመስኖ ልማት በመሰብሰብ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙም አርሶ አደሮቹ አስረድተዋል። በዞኑ በ2009 በመስኖ ከለማው ከ102 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት 15 ሚሊዮን 846 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት መገኘቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም