የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 755 ተማሪዎችን አስመረቀ

84
ሀረር ሀምሌ 30/2010 የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የጤና መስክ ያሰለጠናቸውን 755 ተማሪዎች በመጀመርያ ዲግሪና በደረጃ 4 እና 5 ትምህርት ፕሮግራም ትናንት አሰመረቀ፡፡ ኮሌጁ በመደበኛውና በተከታታይ የትምህርት ፕሮግራም ከሁለት እስከ አምስት ዓመት አሰልጥኖ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 464 በመጀመርያ ድግሪ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና በደረጃ አራትና አምስት ትምህርት የተመረቁ መሆኑን የኮሌጂ ዲን አቶ ድሪባ ገብረየሱስ ገልጸዋል። ተመራቂዎቹ ከኦሮሚያ፣ ድሬዳዋ አሰተዳደር፣ ሐረሪ ፣ ከሶማሌ ፣ አፋር፣ ጋምቤላና፣ ቤንሻንጉል ክልል ተወጣጥተው በኮሌጁ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ ይህም ኮሌጁ በታዳጊ ክልሎች በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ተመራቂዎቹ በአዋላጅ፣ ፐብሊክ ፣ ኢመርጀንሲና ክሊኒካል  ነርስ ፣ በህክምና ላብራቶሪ ፣ በፋርማሲ፣ በራድዮ ግራፊ ፣ በአንስቴዝያና በሌሎች የጤና የትምህርት ዘርፍ ትምህርታችውን ያጠናቀቁ ናቸው፡፡ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አብዱማሉክ በክር በወቅቱ እንደተናገሩት መንግስት ብቃት ያላቸው በስነ ምግባር የታነፁ የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት እየሰራ ነው። ኮሌጁ በተለይ  በማደግ ላይ ላሉ ክልሎች በጤናው ዘርፍ የባለሙያ እጥረት እንዳያጋጥም እያከናወነ ያለውን ስራ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡ የእለቱ ተመራቂዎችም በጤናው ዘርፍ የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት የሙያ ስነ - ምግባር በሚያዘው መሰረት ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልግል እንደሚጠበቅባቸው አሰገንዝበዋል። ከተመራቂዎች መካከል በክሊኒካል ፋርማሲ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ተሰፋዬ ብርሃኑ ሀገሩንና ያስተማረውን ህዝብ በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ተመራቂዋ ሙና ኡመር በበኩሏ  በተለይ መንግስት የእናቶችንና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ ፣ ጤና አገልግሎቱን ለማሻሻልና በሸታን አስቀድሞ ለመከላከል ለሚያደርገው ጥረት ስኬታማነት በትኩረት እንደምትሰራ አስታውቃለች፡፡ የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ከ10ሺ የሚበልጡ የጤና ባለሙያዎችን በሰርተፍኬት ፣ በዲፕሎማና በመጀመርያ ድግሪ አሰልጥኖ አሰመርቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም