ከማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ ያለው መንገድ ዘወትር እሑድ ከተሽከርካሪ ነጻ እንደሚሆን ተገለጸ

128

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቅርቡ የተመረቀው ከማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ ያለው መንገድ ዘወትር እሑድ ለግማሽ ቀን ከተሽከርካሪ ነጻ እንደሚሆን ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ''መንገድ ለሰው'' በሚል መሪ ሀሳብ  የእግር መንገድና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በቸርችል ጎዳና ተካሂዷል።

ዛሬ በተካሄደው "መንገድ ለሰው" መርሃ-ግብር ከቸርችል ጎዳና በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ በተመረጡ 15 የተለያዩ ቦታዎች የብስክሌተኞች፣ የእግረኞችና የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ መርሃ-ግብር ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ ያለው መንገድ ዘወትር እሑድ ለብስክሌተኞች፣ ለእግረኞችና ለተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከተሽከርካሪ ነጻ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ይህም ስፖርትዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ልምዱ እየጨመረ የመጣውን የከተማዋን ነዋሪ እንደሚያበረታታ አመልክተው፤ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከርና ለማቀራረብ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ኢንጂነር ብርሃኑ ግርማ ባለፉት ሁለት ዓመታት "መንገድ ለሰው" በሚል መሪ ሀሳብ አማራጭ የትራንስፖርት መንገድ ለመፍጠር፣ የአካል ብቃት ስፖርትን ለማበረታታትና ምቹ አካባቢን ለመፍጠር ሲሰራ እንደነበር ጠቅሰው፤  ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በቀጣይ በአዲስ አበባ የተመረጡ 15 ቦታዎች በወሩ መጨረሻ እሑድ ከተሽከርካሪ ነጻ በማድረግ ለሞተር አልባ ብስክሌተኞች፣ እግረኞችና ለተለያዩ ስፖርተኞች ብቻ ክፍት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ከማዘጋጃ ቤት መስቀል አደባባይ ድረስ ያለው የቸርችል ጎዳና ግን በልዩ ሁኔታ ዘወትር እሑድ እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ነጻ በማድረግ ለሞተር አልባ ብስክሌተኞች፣ እግረኞችና ለተለያዩ ስፖርተኞች ያለንምን ስጋት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው፤ መንገዶችን በዚህ መልኩ ዝግጁ ማድረግ የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ልምድ ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በተለይ ለሱስ ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች ከሱስ እንዲርቁ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህም እንደማሳያ የቀረቡት ባለፈው ዓመት በየአካባቢው ሲካሄድ በነበረው የጤና አካል ብቃት እንቅስቃሴ በተሰሩ ሥራዎችና በወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ብዙ ወጣቶች መለወጥ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም