በኦሮሚያ ክልል በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሴቶችና ወጣቶች ይሳተፋሉ

69

ጅማ/አምቦ ሰኔ 26/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሴቶችና ወጣቶች ተሳታፊ መሆናቸውን የክልሉ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ የሴቶች የዜግነት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በጅማ ዞን ጎማ ወረዳ በሻሻ ቀበሌ ዛሬ ተጀምሯል።

የክልሉ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን በስፍራው ተገኝተው የዛፍ ችግኝ በመትከል መርሀ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል።

ሃላፊዋ በወቅቱ እንደገለጹት መርሃ ግብሩ "የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለሀገር ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ  የሚካሄድ ይሆናል።

በመርሀ ግብሩ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሴቶችና ወጣቶች እንደሚሳተፉ ጠቁመው በመርሀ ግብሩ 20 ሚሊዮን ችግኝ እንደሚተከል አስታውቀዋል።

በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የችግኝ ተከላ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዥን ማስተባበር፣ የመዋዕለ ህጻናት ግንባታና የደም ልገሳ ስራዎች እንደሚከናወኑ አመላክተዋል።

የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ በበኩላቸው በጅማ ዞን ደረጃ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ4ሺህ በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች እንደሚታደሱ አመላክተዋል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህልን ይበልጥ የሚያጎለብት በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የተሳተፉት ወይዘሮ አለውያ አባ መጫ ሴቶች በአካባቢው ያለውን ማንኛውንም ስራ በፍቃደኝነት ለመስራት ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ሙኒራ አባ ጅሀድ በበኩላቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህሊና እርካታ የሚሰጥ በመሆኑ በየአመቱ የተሳተፉ መሆናቸውን አመልክተዋል።።

በተመሳሳይ  የአምቦ ዩኒቨርሲቲ 3ኛውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ- ግብር አካሂዷል።

ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡን በማስተባበር በኤጄሬ ወረዳ ቱሉ ኮርማ በተባለ ይዞታው ላይ ከ3 ሺህ በላይ ችግኝ ተክሏል።

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዠዳንት ዶክተር ባይሳ ለታ ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር  በጉደርና በአምቦም  ከ120 ሺህ በላይ ችግኝ ለመትከል አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ዶክተር ባይሳ እንዳሉት ባለፉት ሁለት አመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከተተከሉ ችግኞች ከ80 መቶ በላዩ በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መካከል ዶክተር መንግስቱ ቱሉነ የተከሏቸውን ችግኞች በአግባቡ ተንከባክበው ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም