መንግስት የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በማጤን የተኩስ አቁም ማድረጉ ተገቢና ወቅታዊ ነው ... የመዲናዋ ነዋሪዎች

84

አዲስ አበባ፤ ሰኔ25/2013(ኢዜአ)መንግስት የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በማጤን የተኩስ አቁም ማድረጉ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

መንግስት ሕግ ለማስከበር ተገዶ በገባበት ጦርነት የህይወት መስዋእትነት በመክፈል የህወሃት አሸባሪ ቡድን ሊያደርሰው የነበረውን አገራዊ ጥፋት መታደግ ችሏል።

በክልሉ ከተደረገው የህግ ማስከበር በኋላም በመልሶ ግንባታና ሰብአዊ ድጋፍ መንግስት ያሳየው ርብርብ የሚያስመሰግነው መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

አሁን ላይ ወቅቱ የእርሻ ጊዜ በመሆኑ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የግብርና ስራውን እንዲያከናውን የተኩስ አቁም አድርጎ ሰራዊቱን ከአካባቢው ማስወጣቱም ተገቢነት ያለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ከመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ወንድምአገኝ ወርቁ እንደሚሉት ባለፉት ስምንት ወራት በሕግ ማስከበር ስራው በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመፈፀም የሚያስችል ሃብት መባከኑ ለማንኛውም ዜጋ ግልጽ ነው።

በመሆኑም አሁን ላይ በሀገሪቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው በርካታ አንገብጋቢ ተግባራት መኖራቸውን ከግምት በማስገባት መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ የወሰደው እርምጃ ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የሕልውና ጉዳይ የሆኑና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የልማት ፕሮጀክቶች ከመደገፍ ረገድ ሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ማድረግ አለበትም ነው ያሉት።

መንግስትም በአካባቢው ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ መረጃዎችን ለሕዝብ በየጊዜው ማሳወቅ ይኖርበታል ብለዋል።

በትግራይ ክልል ሕግ በማስከበር ላይ የነበረው ሰራዊት ላይ የገጠመውን ተግዳሮትና የሕዝቡን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ማስገባቱ አርቆ አሳቢነቱን የሚያመላክት ነው ያሉት ደግሞ አቶ ከበደ አሰሌ ናቸው።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ሃምሳ አለቃ በለጠ ልሳነወርቅ፤ መከላከያ ሰራዊቱ ብሔርና ሐይማኖት የሌለው በመሆኑ በትግራይ አሸባሪውን ህወሓት በመዋጋት በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል።

ሆኖም ለሕዝብና ለሀገር ተብሎ የተከፈለውን መስዋእትነት በክልሉ ህዝብ ዘንድ ያለመረዳትና ትክክለኛ ግንዛቤ አለመኖሩን ታዝበናል ብለዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሰላማዊት ካሕሱ፤ አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ ተጠቅሞ የተፈጠሩ ችግሮችን በማቃለል የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ መስራት ይጠበቅባታል ነው ያሉት።

በትግራይ ክልል የተደረገው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት መሆኑን መንግስት መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም