የመከላከያ ሠራዊት በሱማሌ ክልል ሰላም ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ የሱማሌ ክልል ተወላጆች ገለጹ

68
አዲስ አበባ ሐምሌ 29/2010 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሠራዊት በሱማሌ ክልል ሰላም ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ገለጹ። ከሐምሌ 26 እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም የሱማሌ ክልል ተወላጅ  ዳያስፖራዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ኡስታዞች፣ ሱላጣኖች፣ የወጣትና የሴቶች ማህበራት በክልሉ ወቅታዊና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለሶስት ቀናት በድሬዳዋ ከተማ ውይይት አካሂደዋል። ተሳታፊዎቹ በክልሉ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የፍትህ እጦት፣ ህገ ወጥ እስራትና ብሔር ተኮር የዜጎች የመፈናቀል ዋነኛ አጀንዳዎች አድርገው ተወያይተዋል። የውይይቱን መጠናቀቅ አስመልክተው ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል። "በክልላችን በተለይም በጅግጅጋ ከተማ በዚህ ስርዓት በተለይም በአብዲ  … የሚመራው ሥርዓት…በተለይ የሌሎችን ብሔረሰቦች የኦሮሞን፣ የአማራን፣ የጉራጌንና ወዘተ ብሔረሰቦች ንብረታቸውን በማጥፋት፣በማውደም፣ቤተክርስቲያን በማቃጣል፣ የኦሮሚያ ባንክን በማቃጠል፣ በክልሉ ውስጥ ህግና ስርዓት እንዲጠፋ አድርጓል። በዚህ አጋጣሚ የተወሰነ የሰው ህይወትም ጠፍቷል። ይህንን ተከትሎም ከኢፌዴሪ መንግስት ኃላፊነቱን ለመወጣት በተሰጠው መመሪያ መሰረት የመከላከያ ሰራዊቱ በጅግጅጋና በሌሎች ወረዳዎች ገብቷል። ይህም ቀደም ብሎ በአገር ሽማግሌዎች የቀረበ ጥያቄ ነው። በመሆኑም፡-
  • የፌደራል መንግስት መከላከያ ስራዊት ሰላምን፣ ፍትህን እና ህዝቡ በነጻ እንዲዘዋወር ለማረጋገጥ ያደረገውን ጥረትና የገባበትን ግዴታ ሙሉ ለሙሉ እንደግፋለን።
  • በአሁኑ ሰዓት በዚያው ሂደት ውስጥ በተፈጠረው “ከኔ በኋላ ሰርዶ አይብቀል” በሚል መርህ የክልሉ ፕሬዝዳንት የሚያደርገውን የአጥፍቶ መጥፋት እና ወሮበላዎችን በማደራጀት ህይወታቸው በዚህ አጋጣሚ ላለፈ፣ ንብረታቸው ለወደመባቸው ሀዘናችንን እንገልጻለን።
  • በክልሎች ውስጥ ያሉትን የክልሉ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት፣ ልዩ ፖሊስ፣ ፖሊስ፣ የሚሊሻ አባላት እና የፍትህ አካላት በመሉ ከጨቋኞች ሥርዓት እራሳቸው ተቆጥበው ተልእኮዎቻውን እንዲወጡና ከመከላያው ጎን ሆነው በህዝቡ ውስጥ ያለውን ሰላም እንዲያረጋጉ ጥሪ እናቀርባለን።
  • ለመንግስት ሠራተኞች ለመላው የክልሉ ህዝቦች የምናስተላልፈው መልእክት ይህ አቶ አብዲ ---ስልጣኑን ለማራዘም የሚፈጽመው የአጥፍቶ መጥፋት ስለሆነ ህዝቡና የመንግስት ሠራተኞች አጠቃላይ ሰላም ወዳድ ማህበረሰብ ሰላምን እንዲያረጋጋ፤ ከመከላከያው ደግሞ ቀኝ እጅ ሆኖ ከመከላከያው ጋር እንዲሰራ በዚህ አጋጣሚ እናሳሳስባለን።
  • ለመላው የኦሮሞ ህዝብ የምናስተላልፍው በአቶ አብዲ የተቀሰቀሰው እሳት የሶማሌና የኦሮሞ ህዝቦች  ለብዙ  ዘመናት አብረው  የተዋለዱ በመሆናቸው  በኦሮሞዎች ላይ የሚደረገውን ማንኛውንም ቅጣት እንደ ማንኛውም ሶማሌ ወገን ያዘንን ስለሆነ የኦሮሞ ህዝብም ይህንን ተረድቶ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ ልናሳሳብ እንወዳለን።
  • ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ስርዓት … ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አህመድ ያመጣውን መደመር፣ ሰላም፣ ይቅርታ ያልተቀበለ የብዙ ሺህ ሶማሌ ህዝብ ህይወት የቀጠፈ፣ ደም ያፈሰሰ በመሆኑ ይህን ችግራችን የእኛ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ችግርም ስለሆነ ለኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ችግር የሆነ አካል ስለሆነ  ከጎናችን እንድትቆሙ በዚህ አጋጣሚ ትብብራችሁን እንጠይቃለን።
  • መከላከያን በዚህ አጋጣሚ የምናሳስበው በክልሉ ውስጥ ያሉትን የመንግስት ተቋማት፣ ህዝባዊ ተቋማቶች፣ የግል ተቋማቶችና የህዝቡን ሰላም እንዲረጋጋ ከማንኛውም ጊዜ በኃላፊነት በንቃት በተሞላበት ሁኔታ እንዲሰሩና በክልሉ ውስጥ ካሉት የመከላከያ የደህንነት ተቋማቶች ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ሁኔታና ግዳጅ እንዲወጡ በእኛ በታዳሚዎች ስም እናሳሳብላን።
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም