ሀገራዊ መግባባቱን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት የድርሻየን እወጣለሁ -  የሀገር ፍቅር ቲያትር

101
ሀምሌ 29/2010 በኢትዮጵያ የተጀመረውን ብሄራዊ መግባባት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ኪናዊ ዝግጅቶችን ለማቅረብ  ዝግጅት ማድረጉን የሀገር ፍቅር ቲያትር አስታወቀ፡፡ በሀገር ፍቅር ቲያትር የባህል ሙዚቃ ክፍል ሀላፊው አቶ መምሩ ጫሞ  “ሀገር ፍቅር” እንደ ስሙ በጣሊያን ወረራ ማግስት ጀምሮ የሀገር ፍቅር ስሜትን ለመቀስቀስ እንደተቋቋመ አስታውሰዋል፡፡ አሁንም በህዝቡ ውስጥ የሀገር ፍቅር ስሜትን የሚያጭሩና በአንድነትና በሰላም ላይ ያተኮሩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ “ከመድረክ ጀርባ” የተሰኘው ቲያትር  አንድነትን፣ የሀገር ፍቅር ስሜትንና ከጀርባ ያሉ ፍትጊያዎችን ከማሳየቱም በላይ ችግሮችን ያለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት መፍታት እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት ስለመሆኑ በአብነት አንስተዋል፡፡ በሙዚቃው ዘርፍም ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ሀገራዊ መነቃቃትን የሚፈጥሩ 16 የሚሆኑ ስራዎችን ለመድረክ ማብቃቱን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮ ኤርትራን ግንኙት በተመለከተም ከአቀባበል ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ የነበረውን ዝግጅት ያደመቁ ስራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል፡፡ አሁን በመላ ሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለው ብሄራዊ መግባባትና አንድነት ቀጣይነት እንዲኖረው የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በሀገር ፍቅር ቲያትር የዘመናዊ ሙዚቃ ክፍል ሀላፊው አቶ ሱራፌል አሸናፊ በበኩላቸው ሀገራዊ ጉዳዮችን የሚያነሱ የኪነጥበብ ስራዎች ተቀዛቅዘው መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን እየታየ ያለውን ለውጥ ተከትሎ የሀገር ፍቅርን፣ አንድነትንና ልማትን መሰረት ያደረጉ ስራዎች ብቅ ብቅ እያሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህን በጎ ጅምር ለማስቀጠል ቲያትር ቤቱ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው በዘመናዊ ሙዚቃውም ሆነ በሙዚቃዊ ድራማዎች ሀገራዊ ይዘት ያላቸው ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት አመት ማብቂያ ብቻ በሰላም፣ ፍቅርና መግባባት ላይ የሚያጠነጥኑ ስራዎች ተሰርተው በመገናኛ ብዙኃን መቅረባቸውንም በአብነት አንስተዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም ልክ እንደስሙ የሀገር ፍቅር ስሜትን የሚቀሰቅሱና ትውልዱ የሀገሩን በጎ ገጽታ እንዲገነዘብ የሚያደርጉ ስራዎችን በመስራት ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጅት ማድረጉን አብራርተዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ብሔራዊ መግባባትን ፣ ፍቅርንና አንድነትን የሚያስተጋቡ የኪነጥበብ ስራዎችን ለህዝብ በማድረስ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም