የቤተክርስቲያኗ አባቶች ወደአንድነት መምጣት አገራዊ ተልዕኮዋን ያጠናክራል - ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን

133
አዲስ አበባ ሐምሌ 29/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች እርቀ ሰላም በማውረድ ወደ አንድ መምጣታቸው ቤተክስርቲያኗ ተጠናክራ አገራዊ ተልዕኮዋን እንድትወጣ የሚያግዛት እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ተናገሩ። ላለፉት 27 ዓመታት በባሕር ማዶና በአገር ውስጥ ለሁለት ተከፍለው ሲወጋገዙ የነበሩ የቤተ ክርስቲያኗ ሲኖዶሶች በእምነቱ ተከታዮችና ሊቃውንቶቿ ላይ ሰፊ ችግር ማስከተሉን በትናንትናው ዕለት በሚሌኒዬም አዳራሽ ዝግጅት የታደሙ ሊቃውንት ለኢዜአ ይገልጻሉ። በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪና የአራቱ ጉባኤያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ፤ "ሲኖዶስ ማለት የአንድነት ጉባኤ፤ የአንድነት ማኅበር ማለት ነው" ይላሉ። ሲኖዱስ በቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ መንበርነት በዘመነ ሐዋርያት እንደተጀመረ የሚገልጹት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፤ በኋላም በየአገራቱና ክፍለ አህጉራቱ ሊቃነ ጳጳሳት ሲኖዶስ እያቋቋሙ አብያተ ክርስቲያናትን ሲመሩ መቆየቱን ይተርካሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም መጀመሪያ በግብጽ ፓትሪያርኮች በኋላም የራሷን ፓትሪያርክ በመሾም በአንድ ሲኖዶስ ስትመራ መቆየቷን ያወሳሉ። ይሁንና በታሪክ አጋጣሚ ሲኖዶሱ ለዓመታት ለሁለት ተከፍሎ ቆይቶ ዛሬ ላይ በአምላክ ፈቃድ በአንድ መጠራት መጀመሩን ይገልጻሉ። የሲኖዶሱ ወደ አንድ መምጣትም የሚያስገኘው መንፈሳዊና ዓለማዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ያብራራሉ። በአዲስ አበባ ታዕካ ነገሥት በዐታ ለማርያም ገዳም የቅኔ መምህሩ ፍሬው አሰጌ፤  የሲኖዶሶች መከፋፈል በቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንቶች መካከል ሰፊ ችግር አስከትሎ መቆየቱን ያስታውሳሉ። በጽርዓ ጽዮን ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉት መምህር ልሳነ ወርቅ ብርሃኑም፤ "ቤተ ክርስያኗ ለዓመታት ፓትርያርክ ሳይሞት ፓትርያርክ ሾመች በሚል በዓለም አብያተ ክርስቲያናት መገለል ደርሶባታል፤ እኛም ሃዘን ላይ ቆይተናል" ይላሉ። ቅዱሳን አባቶችና ሲኖዶሶቹ ወደአንድ መምጣታቸውም ለቤተክርስትያኗ ሐሴት የፈጠረና ለሊቃውንቶቿም ብርሃን የፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል። መምህር ፍሬው ከዚህ በፊት ሲኖዶሱ ተከፍሎ ስለነበር ሊቃውንቶች በጣም ከፍተኛ ጭቆና እየደረሰባቸው ነበረ። ክህነት የሚሰጠው ብዕፁ ወቅዱስ አብነ መርቆርዮስ ክህነት የተቀበሉ ሊቃውንቶች ከፍተኛ ጭቆና እንደነበረባቸው አንስተዋል፡፡ መምህር ልሳነወርቅ “አንደነቱ በጎሳና በዘር ሲከፋፈሉ የነበሩ ምዕመናን ወደአንድ እንዲመጡ አድርጓል፤ ይሄ ደግሞ በፍጹም እምነት አምኖበት የወደደው የፈቀደው ነው” ብለዋል። ለአገልግሎትም በየገዳማትም ሆነ በየአድባራት ባሉት አለቆችም ቢሆን የዚህና የዛ ወገንና አጋር ነህ የሚባል ችግር ስለነበረ ሁሉም በሀዘንና በችግር ላይ እንደነበረ ተናግረዋለ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ መሪነት የነበራትና የሊቃውንት መነሻ እንደሆነች የሚገልጹት መምህር ፍሬው፤ ለዓመታት ተኳርፈው የቆዩት አባቶች እርቀሰላም ማውረዳቸው አርኣያነት ያለውና ቤተክርስቲያኗም የሰላምና የፍቅር አገራዊ ተልዕኮዋን እንድትወጣ እንደሚያስችላት ይናገራሉ። ለ27 ዓመታት ብዙ ችግር መድረሱን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ማኅደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉት ሊቀ ጉባኤ አባ ገብረ ማርያም ሙሉጌታ፤ የወቅቱ የፓትሪያርኮችና ሲኖዶሶች አንድነት ለችግሩ መፍትሄ እንደሚሆን ያምናሉ። አባቶችም የተጀመረውን አንድነት አጽንተው ካለድካም ቤተ ክርስቲያን እንዲጠብቁና ሕዝቡንም በትጋት ማገልገል እንደሚገባቸውም ነው የሚገልጹት። 'አንድነት ሃይል ነው' የሚሉት በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ ሊቀ ትጉኃን ደረበ ብርሃኑም፤ ወደፊትም አንድነቱ እንዲጸና ጸሎት ያስፈልጋል ብለዋል። ሊቀ ጉባኤ አባ ገብረማርያም "ኢትዮጵያና ኦርቶዶስክ ቤተ ክርስቲያን ተለያይተው አያውቁም። አሁንም ወደፊትም አባቶቻችን ተደምረው አንድ ሆነው የተዛባውን፤ የተጣመመውን አቃንተው በሰላም በፍቅር በአንድነት ቤተ ክርትያኗን ከወደቀችበት አንስተው የነበረውን  ከዛሬ ጀምሮ ያችግር ይቀረፋል ብዬ አምናለሁ”። አባቶቻችንም ደከመን ሰለችን ሳይሉ ይህቺ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የምትጸልይ ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች ተግተው፤ አንድነታቸውን አጽንተው  ከአባቶቻችን ከቅዱሳን ሐዋሪያት የተሰጣቸውን ቤተ ክርስቲያኔን ጠብቁ ብሎ አምላካችን እግዚአብሄር የሰጣቸውን ክህነቱን ጠብቀው እንዲያገለግሉ፤ህዝቡን እንዲያስተምሩ አስረድተፈዋል። ሊቀ ትጉኃን ደረበ እንደገልጹት “ታላቁ መጽሃፍ ቅዱስ የተለያየች መንግስት አትጸናም እንኳን በህዝብ ቀርቶ”  እና ከዘመናት ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስያን አንድ አድርጋ የያዘች ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ለምዕመናኖችም ሆነ በየገዳመቱ ለሚጸለዩም ሆነ አንድነት ሃይል ነው”። አክለውም አሁንም ለኦርቶዶክስ አማኝ በሙሉ  እንኳን ደስ ያላችሁ እላለሁ፤ ግን ትልቁ ነገር ለአንደነታችን አሁንም ጸሎት ያስፈልገናል ለአገራችን።   ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያኑ ለዚህ ዕለት መምጣት መሪነቱን ለተጫወቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም