ለኢትዮጵያ አንድነትና ብልፅግና ምዕመኑ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት አለበት - የሀይማኖት መሪዎች

84
አዲስ አበባ ሀምሌ 29/2010 ለኢትዮጵያ አንድነትና ብልፅግና ምዕመኑ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እንዳለበት የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች አስገነዘቡ። የሃይማኖት መሪዎቹንም ለአገሪቱ ሰላም፣ አንድነትና ብልፅግና የመሪነት ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። ከሁለት አስርት በላይ ከአገር ወጥቶ በሰሜን አሜሪካ የነበረው ሲኖዶስ በቅርቡ በተደረገ ስምምነት መሰረት ሀምሌ 25 ቀን 2010 ዓ ም ወደ አገሩ መመለሱ ይታወሳል። በዚህም በኢትዮጵያና ሰሜን አሜሪካ ተለያይተው ይኖሩ የነበሩ የሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ ሥነ ስርዓት ትናንት በሚሌኒየም አዳራሽ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ምዕመናንና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ተከናውኗል። የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች ሁለቱን ሲኖዶሶች ልዩነታቸውን በመፍታት ወደ አንድነት መምጣታቸው ለአገራዊ አንድነት የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። በመካከላቸው እርቀ ሰላም እንዲወርድ ለደከሙ አባቶችና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምስጋና በማቅረብ አንድነትና ሰላምን የሚሰብኩ መልዕክቶች አስተላለፈዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ታሪኳንና ኢትዮጵያዊነቷን ጠብቃ የቆየች በመሆኗ ለአገሪቱ ሰላም እንዲሁም ልዩነት ላለባቸው ተቋማት አርያዓ እንደምትሆን ገልጸዋል። የእስልምናን እምነት ወክለው ንግግር ያደረጉት ሀጂ ዑመር እድሪስ እንዳሉት፤ አንድነት በአካል አብሮ በመሆን ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን ልብ ለልብ መገናኘትን ይጠይቃል። አንድነት ሀይማኖታዊና ልማታዊ ተግባር መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም ሲተጋገዝና ሲፋቀር ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌላው አለም ስለሚተርፍ እርቁን ከልብ በማድረግ ለሰላምና ለአንድነት መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ጥሪ አቀርበዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ እና የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዶ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን በእርቅ በመፍታት ለአገሪቱ ልዕልናና እድገት መስራት አለብን ብለዋል። የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ፀሀፊ አሁን ያለንበት የአንድነትና የሰላም ጉዞ ያለምንም ልዩነት ለአገራችን እድገት የምንሰለፍበት ወቅት ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ፍቅርና ሰላምን እየሰበኩ ሲኖዶሶቹ ወደ አንድነት እንዲመጡ በማድረጋቸውም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በታደሙበት የእርቀ ሰላም ሥነ ስርዓት ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም