በመዲናዋ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ከወሰዱ 110 ሺህ በላይ ባለሙያዎች መካከል ብቁ ሆነው የተገኙት 56 በመቶ ብቻ ናቸው---ባለስልጣኑ

152

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2013 (ኢዜአ) በመዲናዋ በዘንድሮው ዓመት የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ከወሰዱ 110 ሺህ በላይ ባለሙያዎች መካከል ብቁ ሆነው የተገኙት 56 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ የትምህርትና ስልጠና ጥራትና ሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ይህን ያስታወቀው የተቋሙን የ2013 እቅድ አፈፃፀምና የቀጣይ 2014 በጀት ዓመት መሪ እቅድ ላይ ዛሬ ባካሄደው ውይይት ላይ ነው።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በዚህን ወቅት በመዲናዋ በዘንድሮው ዓመት ከተለያዩ ተቋማት ለተወጣጡ 110 ሺህ 295 ባለሙያዎች የብቃት ምዘና ማረጋጋጫ ምዘና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ምዘናውን ከወሰዱት መካከል 62 ሺህ 390 ወይም 56 ነጥብ 6 በመቶው ብቁ ሆነው መገኘታቸውን አንስተዋል።

ውጤቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ5 በመቶ መሻሻል አሳይቷል ነው ያሉት።

በመዲናዋ የትምህርትና ስልጠና ጥራት በሚፈለገው ደረጃ ለማሻሻል ከፍተኛ ስራ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ የትምህርትና ስልጠና ብቃትና ጥራትን ለማረጋገጥ ግንዛቤዎችን ከመስጠት ጀምሮ እርምጃ እስከ መውሰድ መድረሱን ጠቁመው፤  ባለፈው ዓመት ብቻ 84 የትምህርት ተቋማት መስፈርት ባለማሟላታቸው ምክንያት እንዲዘጉ መወሰኑን ለአብነት አንስተዋል።

እውቅና ሳያሟሉ በማስተማር ላይ ያሉ 11 የትምህርት ተቋማት ደግሞ በህግ ክርክር ላይ እንደሚገኙም ጨምረው ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ በዘንድሮው ዓመት 750 የትምህርት ተቋማትን መዝኖ ደረጃ መስጠቱንም አክለዋል።

በመዲናዋ ያለውን የትምህርትና ስልጠና ደረጃ ለማሳደግ  በሚደረገው ጥረት ላይ ኅብረተሰቡ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ደግሞ 1ሺህ 165 የትምህርት ተቋማትን ለመመዘንና 165 ሺህ ሰልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ለማድረግም እቅድ መያዙንም ነው ዋና ስራ አስኪያጇ ያወሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም