የሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ርዝራዦችን አድኖ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል-- ኮሚሽኑ

160

ሰኔ 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ርዝራዦችን አድኖ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ማምሻውን ለኢዜአ በላከው መግለጫ ትግራይ ክልል በሚገኘው አቢ አዲ በተባለ አካባቢ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን ርዝራዦች ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ሰራተኛ ላይ ጥቃት መድረሱን ገልጿል።

በጥቃቱ ረዳት አስተባባሪ ዮሃንስ ሃለፎም እና የመኪና አሽከርካሪ ቴዎድሮስ ገብረማርያም በተባሉ ኢትዮጵያዊያን እና ማሪያ ሄርናንዴዝ በተባለች ስፔናዊት ላይ ትላንት በግምት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት በፈፀሙት ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

በዚህም ኮሚሽኑ በደረሰው ጥቃት ሀዘኑን ገልጾ፤ በአካባቢው ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ርዝራዦችን አድኖ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አሸባሪው የህወሃት ቡድን ርዝራዦች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎች ላይ የፈፀሙትን ጥቃት በማውገዝ ለሟቾቹ ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ለጋሽና እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በትግራይ ክልል የፀጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ለሰራተኞቹ ደህንነት ሲባል ማንኛውም እንቅስቃሴ በመከላከያና በፀጥታ አካላት እጀባ መካሄድ እንዳለበት ያስታወቀ ቢሆንም አልፎ አልፎ የተወሰኑ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ያለአጃቢ በተናጠል በመንቀሳቀሳቸው ለመሰል የሽብር ቡድኑ ጥቃቶች እየተጋለጡ ይገኛሉም ብሏል መግለጫው።

በቀጣይም የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ለደህንነታቸው ሲባል ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር ተቀረርበው እንዲሰሩ ኮሚሽኑ አስገንዝቧል።

በአካባቢው ሽብርተኛውን የህወሃት ቡድን ርዝራዦችን አድኖ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኮሚሽኑ በላከው መግላጫ አስታውቋል።

የዓለም ማህበረሰብም ይህንንና ሌሎችም የሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ርዝራዦች የተለመዱ በሰው ልጅ ላይ የፈፀሟቸው ግድያዎች፣ ኢሰብአዊ፣ አሰቃቂና አስነዋሪ ድርጊቶችን በሚገባ ተገንዝቦ ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም