ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄዳቸው የምርምር ስራዎችን ጥቅም ላይ የማዋል ስራ ሊያጠናክር ይገባል

73
አምቦ ሀምሌ 28/2010 የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሚያካሄዳቸውን ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ወደ ተጠቃሚው ለማውረድ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የዩኒቨርሲቲው ባለድርሻ አካላት ገልጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ተወያይቷል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ወረቅነህ መኮንን በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን የህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ በተለይ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በማህጸን በር ካንሰርና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የምርምር ስራዎችን አከናውኖ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን የኒቨርሲቲው ካለው የትምህርት ዘርፍ ብዛትና ከሚያሠለጥናቸው ተማሪዎች አቅም አንጻር ለማህበረሰቡ ያበረከተው የምርምር ስራ በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም አዳዲስ የምርምር ሥራዎችን ወደ ህብረተሰቡ በማውረድ የአካባቢውን ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ፈዬራ ሰንበታ በበኩላቸው ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የስራ እድል እንዲፈጠር ከተለያዩ ፋብሪካዎችና ተቋማት ጋር በጥምረት ሊሰራ  እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ተማሪዎችም ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በየጊዜው ሁኔታዎችን በማመቻቸትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት በየጊዜው የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሠ ቀነአ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የማህብረሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ በዘርፉም በርካታ የህብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ምርምሮችን ቢያከናውንም ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ግን ክፍተት መኖሩን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት፣ ዘርፉን በማጠናከርና በማደራጀት የህብረተሰቡን ችግር በሚፈቱ የምርምር ስራዎች ላይ በማተኮር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ጊዜ 123 የምርምርና 40 የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ብዙነሽ ሚደግሣ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም