በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል

58
አክሱም ሀምሌ 28/2010 በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በሁሉም የገጠር ወረዳዎች የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ እርሻ ማስተባበሪያ መምሪያ አስታወቀ፡፡ ተምቹ በዘጠኝ ወረዳዎች በሚገኙ 105 ቀበሌዎች መከሰቱም ተመልክቷል፡፡ በዞኑ አስተዳደር የእርሻ ማስተባበሪያ መምሪያ የእጽዋት ክሊኒክና ጸረ ተባይ ባለሙያ አቶ ረዳኢ በላይ እንዳሉት ተምቹ በተለያዩ ቀበሌዎች በ4 ሺህ 778 ሄክታር መሬት ላይ በተሸፈነ ሰብል ላይ መጠነኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ አቶ ረዳኢ እንዳሉት ተምቹ በተከሰተባቸው ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ከ14 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ተምቹን በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁን ድረስ በባህላዊ መንገድ ተምቹን ለመከላከል በተደረገው ጥረት 2 ሺህ ሄክታር መሬት ከተምቹ ነጻ ማድረግ መቻሉን ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ ተምቹን በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ ውጤት እያስገኘ በመሆኑም ሕብረተሰቡ አጠናክሮ እንዲቀጥልበት አቶ ረዳኢ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የሀዱሽ ዓዲ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ሙሴ ይሕደጎ በኩላቸው እንዳሉት በአካባቢያቸው የተከሰተውን ተምች አርሶ አደሩ በጋራ ሆኖ በባህላዊ መንገድ መቆጣጠሩን ገልጸዋል፡፡ በሐምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢ ተምቹ በበቆሎ ሰብል ላይ ጉዳት አድርሶ እንደነበር የተናገሩት አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅት የሚያደርሰውን ጥፋት እንዲቀንስ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ " ኬሚካል ከመርጨት አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ ያደረገው የመከላከል ሥራ የተሻለ ውጤት እያስገኘ ነው" ያሉት ደግሞ በቆላ ተምቤን ወረዳ የአዲሃ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ሀጎስ እምባየ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት ተምቹን በመልቀም ለመከላከል ያደረጉት ጥረት የተሻለ ውጤታማ በመሆኑ በሰብላቸው ላይ ሊደርስ የነበረውን ጉዳቱ ቀንሷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም