የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች ዕርቀ ሰላም ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ትምህርት ሊሆን የሚችል ነው

110
አዲስ አበባ ሃምሌ 28/2010 ፖለቲከኞችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች ዕርቀ ሰላም ትምህርት መውሰድ አለባቸው ተባለ። በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የወረደውን ዕርቅ ለማብሰር የተዘጋጀ ፕሮግራም ከ25 ሺህ በላይ ህዝብ በተገኘበት ታላቅ ሃይማኖታዊ ስርዓት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው። የኢትዮጵያ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ፣ አቡነ ማርቆሪዮስ፣ ሊቃነ ጳጳሳት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት እንዲሁም ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ አምባሳደሮች፣ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ዝግጅቱን ታድመዋል። በፕሮግራሙ ዕርቅና ሰላምን የሚሰብኩ ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ዝግጅቶች እየቀረቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስም ፀሎት አድርሰዋል። የእስልምና ተወካይ አባት "የሰው ልጅ ሁሉም በእኩል የተከበረ ነው እንኳን ለዚህ አበቃችሁ" ብለዋል። "አንድነት ማለት ልማታዊና መንግስታዊ ተግባር ነው" በማለት ፕሮግራሙ የተራራቀ ስሜት የተቀራረበበት ስለሆነ ልባዊ ግንኙነት ይሁን የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው "ዛሬ ታላቅ የደስታ ቀን ነው" ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የሰላም መሳሪያ ሆነው ለዚህ ያበቁ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ተወካይ በበኩላቸው "በሃይማኖት፣ በብሔርና በጎሳ ሳንጣላ በአንድነት መቆም አለብን" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የቃለ ህይወት ቤተክርስትያን አባት በበኩላቸውም "በፆታ፣ በቋንቋ በኃይማኖት ሳንለያይ ለአገራዊ ዕድገትና ልማት መስራት አለብን" የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። የኃይማኖት አባቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ያካሄደችው ዕርቀ ሰላም ሞዴል ያደርጋታል የሚል መልዕክት ተጋርቷል። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤቴክርስትያን ሥራ አስከያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ ባስተላለፊት መልዕክት "ቤተ ክርስትያኗ ለኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር፣ ፊደላት፣ ሒሳብና ፍልስፍናን ጨምሮ በርካታ ታሪካዊ ሥራዎችን ስታበረክት ቆይታለች" ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም ለአገሪቱ አንድነት የምታደርገው አስተዋፅኦ አጠናክራ ትቀጥላለች ያሉት አቡነ ዲዮስቆሮስ የኢትዮጵያ ወጣቶች በሙሉ ያለ ምንም ልዩነት የአገራቸውን መልካም ገጽታ መለያ የሆኑትን መከባበርና አብሮነትን በማገልበት ላይ እንዲሰሩ መክረዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱም የኢትዮጵያን ነፃነትና ሉአላዊነት የሚጋፋን ነገር ሁሉ ለድርድር አቅርባ አታውቅም አሁንም እየሰራች ትቀጥላለች ብለዋል። የዕርቅ ማብሰሪየና የምስጋና ፕሮግራሙን እየመራ የሚገኘው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የቤተ ክርስቲያኗ ካደረገችው ስኬታማ ዕርቅ ትምህርት መውሰድ አለባቸው። በቅዱሳን አባቶች መሀከል ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀው ልዩነት በሦስት ሰዓታት ውስጥ መፈታቱን ዲያቆን ዳንኤል አድንቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ብፁአን አባቶች ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ተነሳሽነት ወስደው ያደረጉት ጥረት ትልቅ ሚና መጫወቱን ዲያቆን ዳንኤል ገልጿል። ይሄን ተከትሎም በአራተኛው ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራውና በሰሜን አሜሪካ በስደት ይኖር የነበረው ሲኖደስ ወደ አገር ቤት እንዲመለስ ሆኗል። የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የዕርቅ ማብሰሪያና የምስጋና ፕሮግራሙን ዝግጅት ከሚሊኒየም አዳራሽ በቀጥታ በማስተላለፍ ላይ ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም