በጂግጂጋ ከተማ የተከሰተውን ብጥብጥ ለማስቆም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ጠብቆ እርምጃ እንደሚወስድ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ

6566

አዲስ አበባ ሀምሌ 28/2010 በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ የተከሰተውን ብጥብጥ ለማስቆም  ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ዛሬ ማምሻውን ለኢዜአ በላከው መግለጫ በክልሉ በተከሰተ ሁከትና ብጥብጥ የህዝቡ ሰላም እና ደህንነት አደጋ ውስጥ እየገባ በመሆኑ   የመከላከያ ሰራዊቱ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደሆነችና ለውጡም መላ የኢትየጵያ ህዝቦችን ባሳተፈ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሷል።

እየተካሄደ ካለው የለውጥ እንቅስቃሴም መላው የአገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ በመሆናቸው ተሳትፏቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ ብሏል።

ሆኖም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የብጥብጥና የሁከት ድርጊቶች ይስተዋላሉ ያለው ሚኒስቴሩ እነዚህ ህገወጥ ድርጊቶች በሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ሃይሉ ከህዝቡ ጋር ሆኖ የማረጋጋት ሥራ በማከናወን ላይ አንደሚገኝም አመልክቷል።

የአገር መከላከያ ሠራዊታችን ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የተከሰተውን ሁከት በቅርበት ሲከታተል፣ ሁኔታውን ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ የነበረ ቢሆንም ብጥብጡ በተፈለገው ፍጥነት ሊቆም እንዳልተቻለም ጠቅሷል።

 ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

አገራችን ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደሆነች ይታወቃል። ለውጡም መላ የኢትየጵያ ህዝቦችን ባሳተፈ እና ባለቤት ባደረገ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል። እየተካሄደ ካለው የለውጥ እንቅስቃሴም  መላው የአገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ በመሆናቸው ተሳትፏቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ።

ሆኖም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች አልፎ አልፎ የብጥብጥና የሁከት ድርጊቶች ይስተዋላሉ። እነዚህ ህገወጥ ድርጊቶች በሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ሃይሉ ከህዝቡ ጋር ሆኖ የማረጋጋት ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።

በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በጂግጂጋ ከተማ የተከሰተው ብጥብጥ፣ ቀጥሎም ወደ ሌሎች አንዳንድ የክልሉ ከተሞች የተዛመተው ሁከት በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለውና በፍጥነት ሊገታ እና ሊታረም የሚገባው ድርጊት ነው።

የአገር መከላከያ ሠራዊታችን ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የተከሰተውን ሁከት በቅርበት ሲከታተል፣ ሁኔታውን ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ የነበረ ቢሆንም ብጥብጡ በተፈለገው ፍጥነት ሊቆም አልቻለም።

በመሆኑም በክልሉ የህዝቦቻችን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ውስጥ እየገባ ያለበት ሁኔታ በመፈጠሩ  የመከላከያ ሃይላችን ሁከትና ብጥብጡን በዝምታ የማይመለከት መሆኑንና የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በጥብቅ ያሳስባል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር

ሃምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም.