በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጣቸውን የሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች ገለጹ

104
ወልዲያ ሀምሌ 28/2010 ከአነስተኛ መሬት በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በመስኖ በማልማት የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን በሰሜን ወሎ  ጎባላፍቶ እና ራያ ቆቦ ወረዳዎች አርሶአደሮች ገለጹ። በዘንድሮ የበጋ ወራት  በመስኖ ከለማው መሬት ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አመልክቷል። በጎባላፍቶ ወረዳ የቀበሌ 11 ነዋሪ አርሶ አደር ካሳ ከተማ በሰጡት አስተያየት  በቋሚነት ከሚያለሙት ሸንኮራገዳ ሌላ  በሩብ ሄክታር  ማሳ ላይ ድንች አምርተው በመሸጥ 15ሺ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ " በዓመት በመስኖ እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት የራሴንና ቤተሰቤን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ በሻገር ከምርት ሽያጭ ከማገኘው ገቢ በባንክም መቆጠብ ችያለሁ" ብለዋል። በዚሁ ወረዳ የቀበሌ 15 አርሶ አደር ቢረዳው መልኩ በበኩላቸው በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ መስኖን ተጠቅመው ዘንድሮ ያለሙት የበቆሎ ሰብል ከቀለባቸው አልፎ  ለገበያ በማዋል  ከ12ሺ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቀው  ከሚያካሄዱት  የእርሻ ልማት የሚያገኙት ምርት  ለቀለብ ፍጆታቸው እንኳን ስለማይበቃቸው ይቸገሩ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአካባቢየችው ያለውን  የውሃ አማራጭ  ተጠቅመው በዓመት እስከ ሶሰት ጊዜ በማልማት ስድስት ቤተሰባቸው በተገቢው ማስተዳደር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይም በችግር ምክንያት ቤት ይውሉ የነበሩ ህጻናት ልጆቻቸውን  ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ለማስተማር  በቅተዋል። በራያ ቆቦ ወረዳ የቀበሌ ሰባት ነዋሪ አርሶ አደር አከለ አሰፋ እንዳሉት ሩብ ሄክታር በሚሆን የመስኖ መሬታቸው ዘንድሮ በቆሎ አልምተው አሁን ምርቱን እየሰበሰቡ ነው። አካባቢያቸው በቆላ በመሆኑ በየዓመቱ በድርቅ ስለሚጠቃ የመስኖ ልማት ለሕይወታቸው መሻሻልና መለወጥ በአማራጭ መፍትሄነት በመጠቀም ላይ ይገኛሉ። ከስድስት  ዓመት በፊት በነበረው ድርቅ  እርዳታ ጠባቂ እንደነበሩ አስታውሰው  አሁን ላይ የመስኖ ልማት በመምጣቱ   የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጡ  ምቹ ሁኔታ እንደፈጠራላቸው ገልጸዋል። በዞኑ  ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ሞገስ ሙሉየ እንደገለጹት በተጠናቀው በጀት ዓመት በመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር መስኖ ከ80ሺ ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል። በልማቱ የተሳተፉ  ከ211ሺ በላይ አርሶ አደሮች በምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በማገዝ ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምግብ ሰብል በማምረት ተጠቃሚ ሆነዋል። የብእርና የአገዳ እህል ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና በርበሬን በመስኖው ለምቶ ከተሰባሰበው ምርት ውስጥ ይገኝበታል፡፡ እንደባለሙያ ገለጻ በየዓመቱ በመኸር ወቅት ከ239ሺ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን የሚገኘው ምርት ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል አይበልጥም፤ የዝናብ አጠር ለሆነው ሰሜን ወሎ ዞን  መስኖ አማራጭ በመሆን የተሻለ ውጤት እያስገኘ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም