ለጠንካራ ሃገራዊ አንድነት ቀጣይነት መረጋገጥ የመራጩ ድምጽ ወሳኝ ነው…የድሬዳዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ

67

ድሬዳዋ ሰኔ 14/2013(ኢዜአ) ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ያለው መንግስት ለመመስረትና ለሃገር አሸናፊነት መራጮች ድምጻቸውን በመስጠት መብታቸውን ሊጠቀሙ እንደሚገባ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ በከዚራ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፃቸውን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት የዘንድሮ ምርጫ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የምትሸጋገርበት ታሪካዊ ቀን ነው።

በዚህም የምርጫ ካርድ የወሰደ የኢትዮጵያ ዜጋ በሙሉ ድምፁን ለሚፈልገው ፓርቲ በመሰጠት ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"እኔም ዴሞክራሲያዊ መብቴን ተጠቅሜ መርጫለሁ" ያሉት ምክትል ከንቲባው መራጩ ህብረተሰብ ሃገር አሸናፊ በምትሆንበት በዘንድሮው ምርጫ በመሳተፍ የዜግነት መብቱን በአግባቡ ሊጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር በገጠርና በከተማ በተዋቀሩ 265 ምርጫ ጣብያዎች እየተከናወነ ለሚገኘው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ አስተዳደሩ ለምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ከንቲባው ተናግረዋል።

በድምፅ መስጠቱ ላይ የተሳተፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ አስተዳደር አገረስብከት ስራአስኪያጅ ሊቀ ትጉሀን ማትያስ በቀለ የዘንድሮ ምርጫ የአገሪቱን ትንሳኤ የሚረጋገጥበት መሆኑን ተናግረዋል።

የአገር አንድነትና ሰላም በመጠበቅ የበለፀገችና የለማች አገር በአንድነት ለመገንባት ሁሉም ተባብሮ መስራት እንደሚገባው ነው የገለፁት።

በዘንድሮ ምርጫ የተሳተፉትን በሙሉ የእንኳን አደረሳቹሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው በውድድሩ የተሸነፈው ያሸነፈውን በማገዝ ለአገር ዘላቂ ጥቅም በጋራ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም