በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ሁለት ምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ አሰጣጥ ዘግይቶ ተጀምሯል

80

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2013(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ 336 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በምርጫ ጣቢያ 5 እና 26 ድምፅ አሰጣጡ ዘግይቶ ተጀምሯል።

መራጮች ለሚፈልጉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት ከንጋቱ 11:30 ጀምሮ ነው በጣቢያዎቹ የተገኙ ቢሆንም ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የደረሰው የክልል ምርጫ የድምጽ መስጫ ጥራዝ የቦሌ ክፍለ ከተማ በመሆኑ በማስተካከል ሂደት መዘግየቱ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ  የጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚዎች ገልፀዋል።

 የክፍለ ከተማው የድምጽ መስጫ ጥራዝ እንዲመጣ ተደርጎ መራጮች ድምጻቸውን መስጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በክፍለ ከተማው ምርጫ ጣቢያ 5 አዳነች አቤቤ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ፣ አቶ ዘላለም ሙላቱ ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ ችግኝ ተክለዋል።

በጣቢያው ዶክተር አርሃም በላይ እና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ በምርጫ ጣቢያው ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ያሳርፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እነዚህና ሌሎች የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎችም ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ በምርጫ ጣቢያው ችግኝ ይተክላሉ።

እየተካሄደ ባለው 6ኛው አገራዊ ምርጫ በአዲስ አበባ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 15 የፖለቲካ ፓርቲዎች  ለ23 መቀመጫ  223 ዕጩዎችን  አቅርበዋል።

ከቀረቡት ዕጩዎች 48 ሴቶች፣ 175 ወንዶች ሲሆኑ በዚህ ውስጥ ሁለት አካል ጉዳተኞች ተካተዋል፤ ሁለት የግል ዕጩዎችም ቀርበዋል።

ለአዲስ አበባ የክልል ምክር ቤት ደግሞ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፤ የግል ዕጩ ተወዳደሪ አልቀረበም።

ለክልል ምክር ቤቱ 868 ዕጩዎች የቀረቡ ሲሆን 234ቱ ሴቶች፣ 634 ወንዶች ናቸው፤ ከእነዚህ መካከል 13 የአካል ጉዳተኞች ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል  ምክር ቤቶች በድምሩ 1ሺህ 91 ዕጩዎች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም