ኅብረተሰቡ የወሰደውን ካርድ ማባከን የለበትም - የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

54

ሰመራ፤ ሰኔ 14/2013 (ኢዜአ) ሕዝቡ ድምጹን ለሚፈልገው ፓርቲ በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብቱን መጠቀም እንዳለበት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሃዋሳ ከተማ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

የእያንዳንዱ መራጭ ድምጽ ለመንግስት ምስረታ ትልቅ ዋጋ አለው ያሉት አቶ ደስታ ሕዝቡ ይህንኑ ተገንዝቦ በወሰደው ካርድ ድምጹን እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም የሚፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ በነቂስ መውጣቱን መመልከታቸውንም ገልጸዋል።

መራጩ ሕዝብ በተረጋጋ ሁኔታ ድምጹን እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ አሁንም የምርጫ አስፈጻዎች የሚሉትን በመስማት ድምጹን መስጠት መቀጠል አለበት ብለዋል።

አገራዊ ምርጫው ሕዝቡ ነፃነቱን ያወጀበት ሂደት ነው፤ ይህም ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ምርጫዎች የተለየ ያደርገዋል ነው ያሉት።

አቶ ደስታ ድምፅ ሰጪዎች በተዘጋጀላቸው ቦታ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያኖሩም ጠይቀዋል።

ምርጫው ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያና ፍትሃዊ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም