በአማራ በተለያዩ ከተሞች ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተጀምሯል

78

ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ታቦር፣ ባህር ዳር ሰኔ 14/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ለ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ጣቢያዎች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ክፍት ሆነው የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ተጀምሯል።

በጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ታቦር፣ ባህር ዳር ከተሞች ከማዳው 12 ሰአት ጀምሮ ምርጫ ጣቢያዎች ክፍት ሆነው መራጩን ህዝብ ማስተናገድ ጀምረዋል።

በጎንደር ከተማ በ220 ምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተጀምሯል።

በተለይም በምርጫ ክልል አንድ ዋርካ ምርጫ ጣቢያ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በርካታ መራጮች በተገኙበት ድምፅ አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ተጀምሯል።

በምርጫ ጣቢያው የምርጫ አስፈፃሚዎች፣ የምርጫ ታዛቢዎችና የፓርቲ ወኪሎች በተገኙበት የምርጫ ቁሳቁሶች መሟላታቸው ተረጋግጦ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተጀምሮ ተጀምሯል።

እስከ ምሽት 12 ሰዓት በሚዘልቀው የመራጮች ድምፅ አሰጣጥ ሂዳት በከተማው 157 ሺህ ነዋሪዎች ድምፅ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ በደሴ ከተማ 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ መራጮች ድምፅ መስጠት ጀምረዋል።

በደሴ ምርጫ ክልል ዳውዶ ምርጫ ጣቢያ ''ሀ'' እና ''ለ'' እንዲሁም ሆጤ ምርጫ ጣቢያ ከማለዳው  12 ሰአት ላይ  መራጮች ድምፅ መስጠት ጀምረዋል።

በደሴ ከተማ አስተዳደር 104 ምርጫ ጣቢያዎች 82 ሺህ 177 መራጨች በወሰዱት ካርድ ዛሬ ወኪሎቻቸውን ይመርጣሉ።

በምርጫው 11 ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እየተፎካከሩ ይገኛሉ።

በተመሳሳይ በደብረ መርቆስ ከተማ ቀበሌ 04 ምርጫ ጣቢያ አንድ እና ቀበሌ 05  ምርጫ ጣቢያ  ሰባት ህብረተሰቡ ከጥዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ እየሰጠ ይገኛል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን በ1 ሺህ 451 ምርጫ ጣቢያዎች 856 ሺህ 189 መራጮች ተመዝግበው በዛሬው እለት ድምፅ መስጠት ጀምረዋል።

እንዲሁም በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፋርጣ ምርጫ ክልል አንድ ስር በሚገኙ በስድስት ምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ድምፅ መስጠት ጀምረዋል።

በደብረ ታቦር ከተማ ፋርጣ ምርጫ ክልል አንድ ስር በ92 ጣቢያዎች ከ55 ሺህ በላይ ህዝብ ድምፅ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ 137 ሺህ 888 ህዝብ ለመራጭነት የተመዘገበ ሲሆን በዛሬው እለትም ከጥዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ የመስጠት ስነ ስርዓት ተጀምሯል።

በተለይም በከተማው ፍኖተ ምርጫ ጣቢያ መራጩ ህዝብ ከጥዋቱ ጀምሮ ድምፁን እየሰጠ ይገኛል።

በከተማው ዘጠኝ ፓርቲዎች እየተፎካካሩ ይገኛል።

በአማራ ክልል ለ6ኛው ሃገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ በ138 ምርጫ ክልልች ስር በተቋቋሙ 11 ሺህ 464 ጣቢያዎች የተመዘገበ  ከ7 ነጠብ 3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በዛሬው እለት ድምፅ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም