ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው

68

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ከማለዳው በ12:00 ሠዓት እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተሮች በተገኙባቸው ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደቱ በሠዓቱ መጀመሩን ታዝበዋል።

ሪፖርተሮቹ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ አቃቂ ቃሊቲና የካ ክፍለ ከተሞች፤  በአማራ ክልል ደብረብርሃንና ቻግኒ፤ በኦሮሚያ ቢሾፍቱ ሱሉልታና እና አምቦ ከተሞች ድምፅ እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

መራጮች ከሌሊቱ ዘጠኝ ሠዓት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ምርጫው የሚጀመርበትን ሠዓት ሲጠባበቁ ቆይተዋል።

ምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ቀደም ብለው በመገኘት የምርጫ ሳጥን ያልተከፈተ መሆኑን፣ ሰነዶች በትክክል መሟላታቸውን በማረጋገጥ ቃለ ጉባዔ ተፈራርመው ድምፅ መስጠት መጀመሩን ሪፖርተሮቻችን አረጋግጠዋል።

በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሚገኛው የቻግኒ ምርጫ ክልል ሰባት ፓርቲዎች ይወዳደሩበታል።

የኢዜአ ሪፖርተር በቻግኒ ምርጫ ክልል ምርጫ ጣቢያ 03-2ሀ እንደተመለከተው ለድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ አስፈላጊ ዝግጅት ተጠናቆ ድምፅ መስጠት ተጀምሯል።

በቻግኒ የምርጫ ክልል 72 የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን 49 ሺህ ሰዎች ድምጽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

በኦሮሚያ ክልል አምቦ ቁጥር 1 ምርጫ ክልል ማለዳ 12 ሠዓት ድምፅ መስጠት ተጀምሯል።

በምርጫ ጣቢያ 04-ሀ2 የተገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ምርጫውን ለማካሄድ አስፈላጊ ነገሮች በሙሉ ተሟልተው ድምጽ መስጠት መጀመሩን አረጋግጧል።

የሱሉልታ ከተማ መራጮች ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ የአረንጓዴ አሻራቸውን ለማሳረፍ ችግኝ እየተከሉ ነው።

በከተማዋ 15 የምርጫ ጣቢያዎች 22 ሺህ 500 መራጮች ድምፅ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም