ወጣቶች በምርጫው ዕለት ለአካባቢያቸው ሠላም በጋራ ሊሰሩ ይገባል - በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች

47

ሰኔ 13/2013 ወጣቶች በምርጫው እለት የአካባቢያቸውን ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ ተግባር በጋራ እንዲሰሩ በአዲስ አበባ የፈረንሳይ አካባቢ በጎ ፈቃደኞች ጠየቁ።

በአካባቢው ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ በጎ ፈቃደኛ ሴቶችና ወጣቶች ለነገው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊነት በቅንጀት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው ምርጫ ጣቢያ-2 የነበሩ በጎ ፈቃደኞች ለኢዜአ እንደገለጹት በምርጫው እለትም ሆነ ከምርጫ በኋላ የአካባቢያቸውን ሠላም በተደራጀ መልኩ የማስጠበቅ ተግባር የዜግነት ግዴታ በመሆኑ ለዚሁ ስኬት እየሰሩ ነው።

በጎ ፈቃደኛዋ ወይዘሪት ዓለምፀሐይ ወርቁ ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ ከወጣቶች ጋር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ተናግራለች።

በዋናነት ወጣቱ አገርና ሕዝብን በሚጠቅሙና ዴሞክራሲን በሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ አተኩሮ እንዲንቀሳቀስ ተደራጅተን እየሰራን ነው ብላለች።

በተጨማሪም ነገ በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መራጮች ርቀታቸውን ጠብቀውና ሳኒታይዘር ተጠቅመው እንዲመርጡ የማስተባበር ተግባር በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንደሚካሔድ ነው የገለፀችው።

ምርጫው አገር የሚመሩ አካላት የሚወከሉበት በመሆኑ በተለይ ወጣቱ በንቃት ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ በማመን በፈቃደኝነት እየሰሩ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት አሸብር ኃይሉ ነው።

ከበጎ ፈቃደኞች ጋር የስራ የተሰማሩት የአካባቢው አዛውንት አቶ ሐይሉ ደገፋ በበኩላቸው ወጣቶቹ ለአካባቢው ሠላም ከነዋሪው ጋራ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው 200 የሚደርሱ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከምርጫ በኋላ ለሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ ተግባር ጉድጓዶችና ችግኞችን በማዘጋጀት ሥራም ተሳትፈዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም