ተመራቂዎች በአገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ በመሳተፍ አገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸው ተገለፀ

66
አዲስ አበባ ሀምሌ 28/2010 ተመራቂዎች በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ እራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውንና አገራቸውን ለማገልገል በታማኝነት መሳተፍ እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡ አድማስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 7 ሺህ 358 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪና በቴክኒክና ሙያ አስመርቋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሞላ ጸጋይ በምርቃው ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በአገሪቱ ብቁ የሰው ኃይል በማምረት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ተመራቂዎች በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ አገራቸውን ለማገልገል በታማኝነት መሳተፍ አለባቸውም ብለዋል። በዩኒቨርሲቲው እየሰለጠኑ የሚገኙ ተማሪዎች ለአገሪቷ ዕድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው ባገኙት እውቀት አገራቸውን ለማገልገል እንደተዘጋጁ ተናግረዋል። ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ወጣት ጽጌብርሃን ስንታየሁ በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ ለስራ የሚያነሳሳና ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ የበለጠ አስዋጽኦ ለማበርከት እንደሚያግዘው ተናግሯል። ሌላዋ ተመራቂ ተማሪ እየሩሳሌም አስናቀ በበኩሏ ባገኘችው ዕውቀት ለመስራትና አገሯን ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች። በገበየችው እውቀት ለመስራት አልያም የራሷን ስራ ፈጥራ ለመስራት እንደምትፈልግም ተናግራለች። ከተመራቂዎቹ መካከል ከ2 ሺህ 300 በላይ በዲግሪ፣ 5 ሺህ 53 ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት መርኃ ግብሮች የሰለጠኑ ናቸው። ዩኒቨርሲቲው ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም