ዓለም አቀፉ ኤሲሲ የአቪዬሽን ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ

148
አዲስ አበባ ሀምሌ28/2010 ዓለም አቀፉ የኤርፖርት አማካሪዎች ምክር ቤት ኤሲሲ የአቪዬሽን ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በጋራ መስራት የሚያሰችለውን ውል መፈረሙን አስታወቀ። ኩባንያው የአውሮፕላን ኪራይን፣ የአየር ትራንሰፖርት ሥራ አመራርን እና ማማከርን ጨምሮ  በተለያዩ የአቪዬሽን ኢንደስትሪ ዘርፎች አገልግሎቱ የሚታወቅ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። ኩባንያው በገባው ውል መሰረትም የኢትዮዽያ አየር መንገድ በአውሮፓ የሚያከናውናቸውን ከበረራ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ተግባራትን  በወኪልነት ያስፈፅማል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሂትሮው፣ ባርሴሎና፣ ፓሪስ፣ ፍራንክፈርት፣ ብራሰልስ፣ ሚላን እና ጄኔቫ ከተሞች በኤርባስ 350፣ በቦይንግ 787-8 እና  787-9 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች የሚሰጠውን የበረራ አገልግሎቶች ኩባንያው ወኪል ሆኖ ያስተዳድራል። የኢትዮዽያ አየር መንገድ የግብይት ክፍል ኦፊሰር አቶ ቡሽራ አወል የኢትዮዽያ አየር መንገድ ከኤ ሲ ሲ ጋር የገባው ውል አየር መንገዱ በአውሮፓ ውስጥ ያለውን ገበያ ለማጠናከር ሰፊ አድል እንደሚፈጥርለት ተናግረዋል። የኤ ሲ ሲ አቪየሽን ኩባንያ ዳይሬክተር ሪካርድ ስሚዝ በበኩላቸው በኩባንያውና በኢትዮዽያ አየር መንገድ መካከል ያለው የትብብር ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው አዲሱ የውክልና ስምምነትም በአውሮፓ የአየር በረራ ገበያ ውስጥ ምቹ የቻርተር አገልግሎቶችን እና የኪራይ እድሎችን በመለየት ተጨማሪ ጥቅም እንደሚያስገኝ ገልፀዋል። በተያያዘ ዜና የህንድ አየር መንገድ ከኢትዮያ አቻው ጋር ያለውን መንገደኞችን ለመለዋወጥ ማቀዱን አስታውቋል። በሁለቱ አገራት አየር መንገዶች ስመምነት መሰረትም የህንድ አየር መንገድ ተሳፋሪዎች በኢትዮዽያ አየር መንገድ በኩል የአፍሪካ መስመሮችን መጠቀም ይችላሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በህንድ አቻው በኩል የአውስትራሊያ፣ ሆንግ ኮንግና የህንድ የሀገር ውስጥ የበረራ መስመሮችን መጠቀም ይችላል። የዚህ ዓይነቱ የበረራ ስምምነት በሀገራቱ መካከል ጠንካራ የኢንቨስትመንትና ንግድ ግንኙነት አንዲፈጠር አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆኑም ተመልክቷል። የኢትዮጵያና ህንድ አየር መንገዶች በትብብር መስራት የጀመሩት በአውሮፓዊያኑ 2011 ዓመት ጀምሮ ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም