የሚበጀንን በመምረጥ ጠንካራ ሀገርን ለማስቀጠል ተዘጋጅተናል ---የመቱና የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች

50

መቱና ጊምቢ ሰኔ 14/2013 (ኢዜአ) በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚበጃቸውን በመምረጥ ጠንካራ ሀገርን ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአሉባቦርና የምዕራብ ወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ መንግስት በመመስረት ሂደት ውስጥ የእያንዳንዱ ዜጋ ድምጽ ዋጋ አለውም ብለዋል፡፡

የመቱ ከተማ ነዋሪ አቶ ሐሰን ሲራጅ እንዳሉት ሀገርን ያስቀጥላል፤ ዲሞክራሲን፣ ልማትንና ሰላምን በሀገሪቱ ያረጋግጣል ብለን የምናምነውን ለመምረጥ ተዘጋጅተዋ፡፡

“ይህ ምርጫ የሰላም፣ የዲሞክራሲ፣ የልማት እንዲሁም ሀገርን የመገንባት ጉዳይ እንደመሆኑ ድምጽ ለመስጠት የሚያስችለንን ካርዳችንን በአግባቡ ተጠቅመን የድርሻችንን መወጣት አለብን”ብለዋል።

“የአንድ ሰው ድምጽ ወሳኝ ነው” የሚለው ወጣት ሌንጮ ገዘኻኝ ደግሞ ነገ መንግስት ሆኖ ሀገርን የሚመራ አካል በእያንዳንዱ ዜጋ ድምጽ ተመርጦ የሚመጣ እንደመሆኑ በጉጉት የሚጠብቀው ነው።

ሁሉም ዜጋ ሀገርን የሚመራን አካል በመምረጥና የነገን ሀገር በማስቀጠል ውስጥ ድምጹ ትልቅ ዋጋ እንዳለው አውቆ በኃላፊነት ስሜት በምርጫዉ ላይ መሳተፍ አለበት ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

“መምህር ታሲሳ ኢሳ በበኩላቸው ምርጫ እያንዳንዳችን እንደዜጋ የሚሆነንን መምረጥ የምንችልበት መድረክ እንደመሆኑ ይህንን መብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም ከወዲሁ መዘጋጀት አለብን” ብለዋል፡፡

የምርጫ ቀኑን በጉጉት እየጠበቁት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በምራብ ወለጋ ዞን የጊምቢ ከተማ ነዋሪው አቶ ለታ ቶለሳ ናቸው።

“በዘንድሮው ምርጫም የተሻለች ጠንካራ ሃገርን ለመገንባት ይበጀኛል የምለውን አካል ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ” ብለዋል።

በዚሁ ዞን የቶሌ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዲ ደረጄ በበኩላቸዉ “ እኔና ቤተሰቤ ሰኔ 14 የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫየዞኑን ሁለንተናዊ ለውጥ የምናረጋግጥበት ቀን ስለሆነ በማለዳ ወጥተን ድምጻችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል” ብለዋል።

ከዓመታት በኋላ በሚመጣ ሃገራዊ ምርጫ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሁሉም የወሰደውን ካርድ ሊጠቀምበት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢዜአ ሪፖርተሮች ተዘዋውረው እንዳስተዋሉት በሁለቱም ዞኖች የነገውን ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ለማካሔድ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም