በሲዳማ ክልል ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ሃይሉ ተደራጅቶ እየሰራ ነው- ፖሊስ ኮሚሽን

50

ሀዋሳ፤ ሰኔ 13/2013 (ኢዜአ) የምርጫው ሂደት በሲዳማ ክልል ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ሃይሉ በክላስተር ተደራጅቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

 የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ክብረት ቶጋ እንዳሉት፤  ለምርጫው ሰላማዊነት የክልሉ ፖሊስ  ከጸጥታ ቢሮ ጋር በመቀናጀት በ44 ወረዳዎችና ሃዋሳ ከተማ አስተዳደር እየተንቀሳቀሰ ነው።

በአራት ክላስተሮች ተካፋፍሎ ስራው እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው እሳቸው በሚያስተባብሩት ዳዬ ክላስተር 11 ወረዳዎች እንደሚገኙና በየክላስተሮቹ የሚከናወኑ ተግባራት ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠውን ህግ መሰረት አድርገው ቅድመ ዝግጅት የተደረገባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ክልሉ ከኦሮሚያና ደቡብ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸውና ከዚህ ቀደም የስጋት ቀጠና በነበሩ አካባቢዎች በተከናወኑ  የእርቅና የሰላም ኮንፍረንሶች አካባቢው ሰላም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ያለምንም ስጋት ድምጹን እንዲሰጥ የጸጥታ ሀይሉ ከህዝቡ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢውንም ሆነ የሃገሪቱን ሰላም የማስከበር ሂደት ያለህብረተሰብ ተሳትፎ ውጤታማ ስለማይሆን ህዝቡ  ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ያለውን ቅንጅት አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

የቅድም ምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ መሆኑንና ይህም በድህረ ምርጫም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የበንሳ ወረዳ ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እጅጉ ቦቶ በበኩላቸው፤ በወረዳው በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የጸጥታ አካሉ መሰማራቱን ገልጸው ስራው ከህብረተሰቡ በተጨማሪ የሃይማኖት መሪዎችንና የሃገር ሽማግሌዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡

በየቀበሌው የመረጃ ወኪሎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ችግር ሲጋጥመው ጥቆማ ፈጥኖ እንዲሰጥና የድምጽ አሰጣጡን በሰላማዊ መንገድ አከናውኖ ውጤቱ በቦርዱ እስኪገለጽ በትዕግስት እንዲጠብቅም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም