ኮርፖሬሽኑ የልማት ኘሮጀክቶችን ለማሳካት በመስራት ላይ መሆኑን አስታወቀ

69
አዳማ ሀምሌ 28/2010 በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ  የተያዙ ትላልቅ የልማት ኘሮጀክቶችን ለማሳካት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡ ኮርፖሬሽኑ የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የዋና ዋና ተግባራት እቅድ አፈጻጸምና የ2011 በጀት ዓመት መነሻ እቅድ ላይ በአዳማ ከተማ ውይይት በማካሄድ ላይ ነው፡፡ የኮርፖሬሽኑ  ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃይለመስቀል ተፈራ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ የመንግስትን የግንባታ ፍላጎት መሰረት በማድረግ  በትላልቅ የልማት ፕሮጄክቶች ግንባታ በውድድርና በቀጥታ በመሳተፍ ላይ ነው። በተለይ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተያዙ የልማት ፕሮጄክቶችን ለማሳካት በመንገድ፣ በትራንስፖርት፣ በመስኖ ኘሮጀክቶች፣ በግድብና በደረቅ ወደብ ግንባታ እየተሳተፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ኮርፖሬሽኑ በተለይ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 116 ኪሎ ሜትር የአዳዲስ መንገድ ግንባታ እና  8ሺህ 354 ኪሎ ሜትር የነባር መንገድ ጥገና አከናውኗል፡፡ የህዝቡ የዓመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሆነው የሽሬ እንዳስላሴና ደንቢዶሎ አየር ማረፊያ ግንባታ ሙሉ በሙሉ አጠናቋል፡፡ በውሃ መሰረተ ልማትም የጊዳቦና የርብ ግድብ ግንባታ ፕሮጄክቶች ከ96 በመቶ በላይ የተጠናቀቁ ሲሆን የመገጭ ግድብ ሥራ 34 ነጥብ 8 በመቶ ማከናወኑ ታውቋል፡፡ የኩራዝ መስኖ ልማት ፕሮጄክት አፈጻጸምም ከ86 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን የወልቃይትና አርጆ ዴዴሳ የስኳር ልማት ፕሮጄክቶች የወሰን ማስከበር ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ የበጀት ዓመቱ ክንውን ዝቅተኛ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት እነዚህን የልማት ኘሮጀክቶች በማከናወን ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን  ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመቱ ያገኘው ገቢ ከእቅዱ በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የግብዓት አቅርቦት ችግር ፣ የፕሮጄክቱ ባለቤቶች የወሰን ማስከበር አቅም ውስንነት፣ የማስፈፀም አቅምና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የፀጥታ ችግር ለእቅዱ ማነስ ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም