በምዕራብ ሸዋ ዞን በድምጽ መስጫው ዕለት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

47

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በድምጽ መስጫው ዕለት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፍት ቤት አስታወቀ፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አበበ ኡማ እንዳሉት በድምጽ መስጫው ቀን መራጮች ችግኝ እንዲተክሉ እግጅት ተደርጓል።

እያንዳንዱ መራጭ ስድስት ችግኞችን እንደሚተክልም መታቀዱን ነው የገለጹት።

በምርጫው ዕለት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቁመው፣ ችግኞቹን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች አቅራቢያ የማጓጓዝ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በድምጽ መስጫው ዕለት ለሚተከሉት ችግኞች የመትከያ የጉድጓድ ዝግጅት ሥራም ተጠናቋል ብለዋል፡፡

ምርጫ ለዴሞክራሲ መጎልበት አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ችግኝ መትከልም የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና ለአየር ንብረት የአረንጓዴ ልማት አጋዥ በመሆኑ ህብረተሰቡ ብንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለሚፈልገው እጩ ተወዳዳሪ ድምጹን ከሰጠ በኋላ ችግኝ እንዲተክል ለማድረግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡

በቶኬ ኩታዬ ወረዳ ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ደጀኑ ለኢዜአ እንዳሉት የችግኝ ተከላ ሥራው የሚመራው በየቀበሌው በተመደቡ ባለሙያዎች ነው።

በወረዳውም ለችግኝ መትከያ የሚያገለግሉ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎችም በምርጫው ቀን ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ ችግኝ ለመትከል ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን በ3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 339 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን ከዞኑ ግብርና እና የተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም