የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉዞ ኢትዮጵያዊያንን በአገራቸው የልማት ተግባራት እንዲሳተፉ የሚያስችል ነው-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

77
አዲስ አበባ ሀምሌ 28/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን እውቀት፣ ልምድና ሃብት ለአገራቸው ልማት እንዲያውሉ የሚያግዝ መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ በሰሜን አሜሪካ ሶስት ግዛቶች ተዘዋውረው በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። በውይይታቸውም የሄዱበት የመደመር ጉዞን ከሚጠበቀው በላይ እንዳሳኩ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። በዚሁ ዙሪያ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየት የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሜን አሜሪካ ጉብኝት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው የልማት እንቅስቃሴ በተጨባጭ ተሳታፊ እንዲሆኑ እድል የከፈተ ነው ብለዋል። በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በአገራቸው ባሉ ማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ በያገባኛል መንፈስ ያላቸውን እምቅ እውቀት፣ አቅምና ሃብት እንዲጠቀሙ ትልቅ መነሳሳት የፈጠረ መሆኑን ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች በሰሙት መረጃ መገንዘባቸውን ነው የገለፁት። የኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በአገራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ ማድረግ አገሪቷ ለጀመረችው  የእድገትና ልማት ጎዳና መሳካት ከፍተኛ አስተዋጾ እንደሚኖረውም ነው ያላቸውን ጽኑ እምነት የገለጹት።  ወጣት ንጉሴ አለሌሳ በሰጠው አስተያየት "በሰሜን አሜሪካ ቆይታቸው ብዙ ስራዎች እንደሰሩ ነው ያየነው በሚዲያም የሰማነው፤ በዚህም አጋጣሚ የጥላቻና የቂም የበደል ግንቡን አፍርሰው በፍቅር በይቅርታና በአንድነት ግንቡ እንዲገነባ ተደርጓል። የሰሜን አሜሪካ ቆይታቸውን ብንመለከት ብሔር ብሔረሰቦችን ባሳተፈ መንገድ ያደረጉት ቆይታ አስደሳች ነበር" "መንግስት ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን በእውቀት በጉልበታቸውና በላቸው ሀብት ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ እንደገና ለመመለስ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያሳዩም መንግስት የድርሻውን እንዲወጣ ነው የምፈልገው።"ብሏል፡፡ ˝ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ አገርም ሆነ በአገር ውስጥ  ሁሉ ጥሩ ስኬት ነው የሚያጋጥማቸው፤ በተለይ  በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩልና የኃይማኖት አባቶችን ከማስተባበርና ከማስታረቅ አኳያ የክርስቲያኑ የሙስሊሙንም በጣም የሚያስደስት ቆይታ ነበር፤ በጣም ተደስተንበታል፤ በጣም ጥሩ አካሄድ እየሄዱ ያሉት ሐሳባቸው የሁሉንም ተሳትፎን ያካትታል፤ በመሆኑም ስኬታማ ነው ብዬ አስባለው˝ በሚል የሚገልጹት  አቶ ሻለቃ ቦጋለ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ካሳ የተባሉ የከተማው ነዋሪ እንዳሉት እኔ በበኩሌ በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታ ያደረጉት ነገር ምርጥ ነገር ነው በኃይማኖት አባቶችም ሆነ በዲያስፖራዎችም በኩል ያደረጉት ነገር በአገር ላይ አብረው መጥተው፤ እዚህ ኢትዮጵያ ላይ እንዲሰሩ ማድረግ ማንም ያላደረገውንና ጥሩ ነገር ነው ያደረጉት ብዬ የማስበው˝ ፡፡ አቶ ወንድማገኝ ማሞ በበኩላቸው"ለኔ በጣም የተለየ የምለው ቤተክርስቲያን ስንት ዓመት የተጣሉትን አባቶች አስታርቀው ይዘው በመምጣታቸው በጣም ደስ ብሎኛል። ሁለተኛው ዲያስፖራው እንዲተባበርና በፍቅርና በአንድነት እንዲያምን የሚሰሩት ስራ ደስ ነው ያለኝ። ይህ ለዜጎች ብርታት ይሰጣል"ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በአገራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ ለማድረግ ይዘው የሚመጡትን እውቀት፣ ጉልበትና ሃብት ሥራ ላይ እንዲውል መንግስት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም