የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታዎች ችግራችንን ፈተውልናል.... የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች

62
ሰቆጣ ሀምሌ 28/2010 በአካባቢያቸው ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ለዘመናት የነበረባቸውን የውሃ ችግር እንደፈቱላቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ በተጠናቀቀው የ2010 በጀት ዓመት 253 የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ ውሃና መስኖ ኢነርጅ መምሪያ አስታውቋል፡፡ በዞኑ ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ቀበሌ 17 የሚኖሩት ወይዘሮ ውድ አስረስ  እንዳሉት ከእዚህ ቀደም በአካባቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ባለመኖሩ የምንጭ ውሃ ለመቅዳት የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ ያደርጉ ነበር፡፡ ከምንጭ የሚቀዱት ውሃ ንጽህናው የየተጓደለ በመሆኑ በተለይ ሴቶችና ህጻናት በተደጋጋሚ ለሆድ ሕመም ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰዋል። እንደ ወይዘሮ ውድ ገለጻ  በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ በመገንባቱ ይደርስባቸው የነበረውን የጤና ችግርና እንግልት አስቀርቶላቸዋል፡፡ በጋዝጊብላ ወረዳ ቤላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሻንበል አለልኝ በበኩላቸው ከእዚህ ቀደም የምንጭ ውሃን ያለምንም የውሃ ማጣሪያ ይጠቀሙ እንደነበር ተናግረዋል። ውሃውን ለማምጣት ሴቶችና ህጻናት በርቀት ወደሚገኝ ወንዝ ስለሚሄዱ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ከማባከን ባለፈ ከትምህርት ገበታ ላይ ይቀሩ እንደነበር ተናግረዋል። የተገነቡ የውሃ ተቋማት ይህን ችግራቸውን ስላስቀሩላቸው ዘለቄታዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡን በማስተባበር እንዲጠበቁና ብልሽት ሲያጋጥም በወቅቱ እንዲጠገኑ የማድረግ ሥራ እያከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል። የዞኑ ውሃና መስኖ ኢነርጅ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኘ መብራት ለኢዜአ እንዳሉት በተጠናቀቀው የ2010 በጀት ዓመት 253 አነስተኛ፣ መለስተኛና ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችና ምንጭ የማጎልበት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል ለውሃ ተቋማቱ ግንባታ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተገኘ ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገ ሲሆን በእዚህም 110 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ከተገነቡት የውሃ ተቋማት ውስጥም 28 ያህሉ ምንም አይነት የውሃ አማራጭ በሌላቸው ቆላማ አካባቢዎች በሚገኙ የጤና ኬላዎችና ትምህርት ቤቶች ላይ የጣራ ላይ ውሃ ለማሰባሰብ የውሃ ታንከር የተሰራላቸው መሁኑን አስረድተዋል፡፡ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት የውሃ ተቋማት የዞኑን 44 ነጥብ 7 በመቶ የውሃ ሽፋን ወደ 56 በመቶ ማሳደግ ያስችላል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም