የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች በንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት መቸገራቸውን ገለፁ

70
አክሱም ሀምሌ 28/2010 በአክሱም ከተማ በተከሰተው  የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት መቸገራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ የከተማው ነዋሪ አቶ መብራቱ ወልደትንሳኤ እንዳሉት  በከተማው በሚታየው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እየተዳረጉ ነው፡፡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ለማግኘት ወደ ሌሎች አካባቢዎች በሚያደርጉት ጉዞም ለእንግልትና ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በጋራ እንዲጠቀሙበት በአካባቢያቸው የተሰራው የጋራ መጸዳጃ ቤትም በውሃ እጥረት ምክንያት አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ የበጋሸት አብርሃ  በበኩላቸው በከተማው ጥገና የሚያስፈልጋቸው የውሀ መስመሮች በወቅቱ ስለማይጠገኑ የሚለቀቀው ውሀ ህብረተሰቡ ጋር ሳይደርስ መንገድ ላይ እንደሚፈስ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያንት ለህብረተሰቡ መድረስ የነበረበት ውሃ ለብክነት እየተዳረገ ነው፡፡ በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች መስመር ቢዘረጋም ውሀ እንደማይደርሳቸው የገለፁት አቶ የበጋሸት መንግስት የነዋሪዎችን ጥያቄ በመገንዘብ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ለከተማዋ እድገት የኮንስትራክሽን ስራ ወሳኝ  መሆኑ እየታወቀ በውሃ እጥረት ምክንያት የግንባታ ስራ  እያስተጓጎለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ በየነ ገብረማሪያም ናቸው፡፡ በመሆኑም መንግስት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የአክሱም ከተማ ከንቲባ አቶ ኤልያስ ካህሳይ በከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሀ ችግር መኖሩን አምነው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ ነዋሪዎች የሚያገኙትን ውሃ በቁጠባ እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል፡፡ የአክሱም ከተማ የውሃና ፍሳሽ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ብሩ በበኩላቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ ለከተማው ነዋሪ  ለማዳረስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት መስመር ተዘርግቶላቸው ውሃ የማይደርሳቸው አከባቢዎችን ችግር ለመቅረፍ ተጨማሪ ውሃ ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መስመሮችን ለመጠገንና አዳዲስ የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈር ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ሀላፊው ተናግረዋል፡፡ የጋራ መጸዳጃ ቤቶች አገልግሎት እንዲሰጡም የውሃ መስመር እንዲገባላቸው እየተሰራ በመሆኑ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም