በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከ300ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ለማምረት እየተሰራ ነው

47
ጎንደር ሀምሌ 28/11/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ለውጭ ገበያ የሚቀረብ ከ300ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ በመኸር ወቅት ለማምረት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ ለኢዜአ እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ ሰሊጥ አምራች በሆኑት በታች አርማጭሆና ጠገዴ ወረዳዎች 40ሺ ሄክታር መሬት በሰሊጥ መሸፈን ተችሏል፡፡ በወረዳዎቹ የሰሊጥ ልማቱ እየተካሄደ የሚገኘው በግብርና ኢንቨስትመንት በተሰማሩ ከ1ሺ በላይ ባለሀብቶችና አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶአደሮች ነው፡፡ በሰሊጥ ከተሸፈነው መሬት ከ20ሺ ሄክታር በላይ በመስመር የተዘራ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው " አርሶአደሮችና ባለሀብቶች ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችንና ግብአት መጠቀምን እንዲለማመዱ እየተደረገ ነው " ብለዋል። በዚህም በምርት ዘመኑ በዞኑ ቀድሞ በአማካኝ በሄክታር የሚገኘውን ስድስት ኩንታል ወደ ስምንት ኩንታል ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡ ከሁለቱ ወረዳዎች በተጨማሪ ለሰሊጥ ልማት ተስማሚ ስነ ምህዳር ባላቸው በምዕራብና ምስራቅ በለሳ እንዲሁም በኪንፋዝ በገላ ወረዳዎች ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የሰሊጥ ልማት እየተስፋፋ መምጣቱንም  ጠቁመዋል፡፡ ልማቱ እየተሰፋፋ ባለባቸው ሶስቱ ወረዳዎች በ3ሺ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ (ኦርጋኒክ) ሰሊጥ እየለማ መሆኑንና  ምርቱም በቀጥታ ለአውሮፓ ገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው ተብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ከእነዘሁ  ወረዳዎች ለሙከራ የተላከው 15ሺ ኩንታል ኦርጋኒክ ሰሊጥ በአውሮፓ ገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ በቀጣይም ለሀገራቱ ለመላክ ታቅዷል፡፡ በርካታ የአውሮፓ ካምፓኒዎች ኦርጋኒክ ሰሊጥ እንዲመረትላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ አርሶ አደሮቹ ከማምረታቸው በፊት የሽያጭ ኮንትራት ከካምፓኒዎች ጋር የሚጀመርበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተገልጿል፡፡ በኪንፋዝ በገላ ወረዳ የጭቅቂ ቀበሌ አርሶአደር ግስሙ በላይ በሰጡት አስተያየት አካባቢያቸው ዝናብ አጠር  በመሆኑ ሰሊጥ በባህሪው በአነስተኛ ዝናብ ስለሚመረት ለልማቱ ትኩረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በተያዘው የምርት ወቅት ያላቸውን ግማሽ ሄክታር መሬት በሰሊጥ መሸፈናቸውን የተናገሩት አርሶአደሩ ካላሙት መሬት አራት ኩንታል ሰሊጥ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡ ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶአደር ይስማው ቻላቸው በበኩላቸው “ያለፈው ዓመት የሰሊጥ ዋጋ ከፍ በማለቱ ያመረትኩትን 6 ኩንታል ሰሊጥ በመሸጥ ባገኘሁት ገንዘብ የዓመት ቀለብ ሸምቼ በጋውን ያለሀሳብ መዝለቅ ችያለሁ” ብለዋል፡፡ በተያዘው የምርት ወቅትም አንድ ሄክታር መሬታቸውን በሰሊጥ በማልማት ስምንት ኩንታል ምርት እንደሚብቁ ተናግረዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም