በባህርዳር ከተማ ጉዳት ደርሶበታል የተባለ ድርጅትን ፖሊስ እያጣራ ነው

72
ባህር ዳር ሀምሌ 28/2010 በባህርዳር ከተማ የኤች አይቪ ኤድስና የአባላዘር በሽታ ስርጭት ያለበትን ደረጃ ለማጥናት በተሰማራ ድርጅት ንብረት ላይ በግለሰቦች ደርሷል የተባለውን ጉዳት በማጣራት ላይ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ሞገስ ዕውነቱ ለኢዜአ እንደገለጹት ጉዳቱ የደረሰው ትናንት ማምሻውን በተለምዶ ጎፋ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው የሽምብጥ ክፍለ ከተማ ነው። ግለሰቦች በወሰዱት እርምጃ በአንድ ተሽከርካሪ ላይ ቃጠሎና በሶስት ተሽከርካሪዎች ላይ ደግሞ የመሰባበር ጉዳት ደርሷል፡፡ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንዳሌለ ምክትል ኮማንደር ሞገስ አስታውቀዋል። ጉዳቱ የደረሰው በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር የሚገኝ" ሀርማወር ሀንሰን" የተሰኘ በኤች አይቪ ኤድስ ላይ አተኩሮ የምርምር ስራ የሚያካሂድ ድርጅት ንብረት ላይ  ነው። ድርጅቱ ወደ ጥናት ስራው ከመግባቱ በፊት አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ለህብረተሰቡ ስለጠቀሜታው አስቀድሞ በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደነበረበትም ኃላፊው ገልጸዋል። አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮች ሲያጋጥም እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ተረጋግቶ ለፀጥታ ተቋማት ማሳወቅ እንጂ በስሜት ተገፋፍቶ በሀገር ሃብትና ንብረት እርምጃ ሊወስድ እንደማይገባም አሳስበዋል። የችግሩን መንስኤና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን የማጣራት ስራ ፖሊስ እያከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ግዛቸው ይስማው በበኩላቸው "ሀርማወረሀንሰን "በሀገር አቀፍ ደረጃ ከኤች አይቪ ኤድስ ጋር በተያያዙ የድጋፍና ምርምር ስራዎችን የሚሰራ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል። ተቋሙ በክልሉ ያለውን የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ለማጥናትና ለችግሩ ዕልባት ለመስጠት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት በሆኑ ተጋላጭ ወጣቶች የደም ምርመራ የሚያደረግ  ነው። የድርጅቱ ባለሙያዎች ስራዎችን እያከናወኑ ያለው ከኢንስቲትዩቱና ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ባለሙያዎች በመቀናጀት ፈቃደኛ ከሆኑ ወጣት ሴቶች ደም በመውሰድ የኤች አይቪ የምርመራ ስራ እያካሄዱ እንደነበረም አስረድተዋል። ሆኖም ግለሰቦች ባልተጨበጠ ወሬ የወሰደው እርምጃ ንብረት ከማውደሙም በላይ የጤና ምርምር ስራው እንዲስተጓጎል ማድረጉን  ገልፀዋል። የጥናት ስራው በመንግስት በኩል ሙሉ እውቅና ያለውና በማንኛውም መንገድ ለጤና ጉዳት የሚዳርግ ክትባት አለመሰጠቱንም ዶክተር ግዛቸው አረጋግጠዋል። የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ማሞ ጥናት የሚያደርጉት ባለሙያዎች የቅድመ ዝግጅት ስራ ሲያከናውን ለስድስት ሳምንታት መቆየታቸውን ተናግረዋል። በዚሁ ወቅትም ችግሩ ያለባቸውን አካባቢዎች በጥናት የመለየት ስራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውንና ትናንት ደግሞ የኤች አይ ቪ የደም ናሙና መወሰድ መጀመራቸውን አመልከተዋል። በተሳሳተ ወሬ የተፈጸመው የጥፋት ድርጊት አሳዛኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጸም ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም