የተወሰነባቸው ግብር ገቢያቸውን ያላገናዘበ መሆኑን በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አንዳንድ ግበር ከፋዮች ገለጹ

141
ማይጨው ሐምሌ 27/2010 የተወሰነባቸው ግብር ገቢያቸውን ያላገናዘበ በመሆኑ መንግስት ቅሬታቸውን እንዲያይላቸው በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አንዳንድ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ገለጹ። በኮረም ከተማ በሆቴል ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ኃይለጊዮርጊስ ረዳ እንዳሉት የሚከፍሉት ግብር  አስቀድሞ ለህዝብ ይፋ በመደረጉ ግልጽነትን ያሰፍናል፡፡ ይሁንና በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በከተማው የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ የተዳከመ መሆኑ እየታወቀ 60ሺህ ብር ግብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸው አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ "የተጣለብኝ ግበር የሆቴሌን አቅም ያገናዘበ እይደለም" ያሉት አቶ ኃይለጊዮርጊስ፣ በአሁኑ ወቅት ግማሹን በመክፈል ቅሬታቸውን ለሚመለከተው አካል ማቅረባቸውንና በመንግስት በኩል መፈትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የግብር ውሳኔን አስቀድሞ ለህዝብ በሚታይ ቦታ ላይ መለጠፉ በግብር አወሳሰን ላይ የነበረውን ጥርጣሬ መቅረፉን የተናገሩት ደግሞ በማይጨው ከተማ የመድኃኒት ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ አብረሃ ስዩም ናቸው፡፡ እንዲከፍሉት የተወሰነባቸው የ30 ሺህ ብር ግብር ከገቢያቸው ጋር ተመጣጣኝ ነው ብለው ባያምኑም መክፈላቸውንና መንግስት እንደእርሳቸው ቅሬታ ላለባቸው ግብር ከፋዮች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ "አንዳንድ የቫት ተመዝጋቢዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንድ ነጠላ ደረሰኝ ሳይቋርጡ ከተገኙ 50 ሺህ ብር እንዲቀጡ መደረጉ ተገቢ ባለመሆኑ መንግስት አሰራሩን መልሶ ሊያየው ይገባል" ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት፣ የትራንስፖርትና ሌሎች መሰል ወጪዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ የግብር አወሳሰን አለመሆኑን የተናገሩት ደግሞ በመኾኒ ከተማ በምግብ ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ንጉስ ግርማይ ናቸው፡፡ ዘንድሮ እንዲከፍሉ ከተወሰነባቸው 27 ሺህ ብር ግማሹን በመክፈል ቅሬታቸውን  ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡ የመኾኒ ከተማ ነዋሪ አቶ አብረሀ ኪሮስ እንዳሉት በዚህ  ዓመት የንግድ ሥራው በተወሰነ ደረጃ ቢቀንስም ገቢያቸውን ታሳቢ ያደረገ ግብር እንደተወሰነባቸው ገልጸዋል፡፡ በእንጨት ሥራ እንደሚተዳደሩ የተናገሩት አቶ አብረሀ እንዲከፍሉት የተወሰነባቸው 3 ሺህ ብር ገቢያቸው ያገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዶላር ምንዛሬ ለውጥ ምክንያት በብረት ላይ የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ ገቢያቸው ቢቀንስም የተወሰነባቸው 5 ሺህ ብር ግብር ፍትሃዊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኮረም ከተማ በብረት ንግድ ሥራ የሚተዳደሩ አቶ ሞጎስ አሰፋ ናቸው፡፡ የዞኑ ንግድና ከተማ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስመላሽ ረዳ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ ከሐምሌ 1 እስከ 30 ቀን 2010ዓ.ም  ከደረጃ "ሐ" ንግድ ዘርፍ ለማሰባሰብ ከታቀደው 17 ሚሊዮን ብር አብዛኛው መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር አስቀድሞ ውይይት በማድረግ የግብር ውሳኔው በይፋ መለጠፉ አብዛኛውን ግብር ለመሰብሰብ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ አብዛኛውን ግብር ከፋይ ገቢውን ያገናዘበ ግብር እንዲከፍል መወሰኑ በራሱ በተሻለ ግብር እንዲሰበሰብ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ አቶ አስመላሽ እንዳሉት በዞኑ ከሚገኙ 13 ሺህ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ውስጥ 10 ሺህ ያህሉ ከሐምሌ አንድ እስከ 25 የሚፈለግባቸውን ግብር ከፍለዋል፡፡ ቅሬታ ላቀረቡ ውስን የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ከንግዱ ማህበረሰብና ከመንግስት አካል የተዋቀረ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በማቋቋም ጥያቄዎቻቸውን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም