ሃይቁን ለብክለት እየዳረጉ በሚገኙ ድርጅቶችና ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ተጠቆመ።

74
ባህር ዳር ግንቦት 8/2010 በካይ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ወደ ጣና ሃይቅ በመልቀቅ ሃይቁን ለብክለትና ጉዳት እየዳረጉ በሚገኙ ድርጅቶችና ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ተጠቆመ። በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ 27 ድርጅቶች፣ ተቋማትና ፋብሪካዎች በበካይ ቆሻሻ ሃይቁን እየጎዱ መሆኑ በተካሄደ የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት ኦዲት ተረጋግጧል። በኦዲት ምርመራው የተሳተፉት አቶ ጌታቸው ንጋቱ እንዳሉት  ከየካቲት 23 እስከ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም በ27 ተቋማት ላይ የአካባቢ ብክለት ክትትልና ቁጥጥር ተካሂዶ አብዛኞቹ ተቋማት ሃይቁን እየበከሉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ብክለት እያስከተሉ የሚገኙ ተቋማትና ፋብሪካዎች በጤና እና በአካባቢ ላይ ጉዳት እያደረሱ በመሆናቸው ተገቢው እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡ የኦዲት ግኝቱ በባህር ዳር ከተማ ሲገመገም የማዕከላዊ ጎንደር የአካባቢ ህግ ተከባሪነትና ቁጥጥር ባለሙያው አቶ መርከብ እሸቴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት በሃይቁና በአካባቢው እየደረሰ ያለው ብክለት የሰውን ልጅ ጤና ከመጉዳቱም በላይ በሃይቁ ብዝሃ ይህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኗል። በኦዲቱ የተገኙትንና በቀጣይም ሌሎች ያልተካተቱ ተቋማትን በመከታተል ከሚያደርሱት ጥፋት እንዲታረሙ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት የስራ ሂደት መሪው ኮማንደር ስማቸው ሁነኛው በበኩላቸው በጣና ሃይቅ ላይ ተቋማቱ እያደረሱት ያለው የአካባቢ ብክለት አሳሳቢና ጊዜ የማይሰጠው  ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል። የአካባቢን ደህንነት በኃላፊነት መወጣት ሲገባቸው በግድየለሽነት ጉዳት እያደረሱ ያሉ ተቋማትም ሆኑ ፋብሪካዎች የሚፈፅሙትን የህግ ጥሰት መከላከል እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡ በክልሉ ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ውሃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወርቁ አለሙ እንዳሉት በውሃ አካላቱም ሆነ በአካባቢ ብክለት ህዝቡን ለጉዳት እየዳረጉ የሚገኙ ተቋማት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የባለሙያ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሚደረግላቸው ድጋፍ የማይመለሱ ከሆነ ግን ህግን የማስከበር ስራ መሰራት እንደለበት አስገንዝበዋል፡፡ የአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ  ''ህዝቡ ከብክለት በፀዳና ለጤንነቱ ስጋት በማይሆን አካባቢ የመኖር ህገ መንግስታዊ መብቱ” ሊጠበቅለት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ድርጅቶችም ሆኑ ፋብሪካዎች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት የአካባቢ ተፅኖ ግምገማ ማካሄድና በየጊዜው ማደስ ሲገባቸው ይህን እያደረጉ አለመሆኑ በኦዲት ግኝቱ መረጋገጡንም ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት ፍሳሽንም ሆነ ደረቅ ቆሻሻን አካባቢን በማይበክል መንገድ ማስወገድ እንዳለባቸው አስገዳጅ ህግ ቢኖርም ተቋማቱ ለህጉ ተገዥ አለመሆናቸውን ከግኝቱ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ፍሳሽም ሆነ ደረቅ ቆሻሻን እንዲሁም ኬሚካል ነክ የሆኑ የላውንደሪ ቤት ፍሳሶችን ቀጥታ ወደ ሃይቁ በመልቀቅ እየደረሰ ያለው ጉዳት በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል። ''የአካባቢንና የህዝብን ደህንነት ስጋት ላይ እየጣለ የሚካሄድ ልማት ባለመኖሩ በችግሩ ውስጥ ያሉ ተቋማትም ሆኑ ፋብሪካዎች ከችግራቸው እንዲወጡ” አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰው ከድርጊታቸው በማይቆጠቡ ተቋማትና ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ችግሩ የተገኘባቸው ተቋትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ ምንም ዓይነት የፍሳሽ ማስወገጃ ሳይኖራቸው የሽንት ቤት፣ የላውንደሪና የምግብ ቤት ፍሳሽ በቀጥታ ወደ ጣና ሃይቅና አባይ ወንዝ የሚጨምሩ ተቋትና ድርጅቶች፡- በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ  ዘንዘልማ፣ ይባብና ቴክስታይል ካምፓሶችና የመምህራን መኖሪያ ቤቶች፡-
  • የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ፣
  • ጣና ሆቴል፣
  • ፈለገ ህይዎት ሪፈራል ሆስፒታል፣
  • ሃበሻ ቆዳ ፋብሪካና የከተማው የፍሳሽ ማስወገጃ ቦታ
የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያና  ማጣሪያ ቢኖራቸውም ያልተጣራውን ፍሳሽ ወደ ጣና ሃይቅ የሚለቁ ተቋማትና ድርጅቶች፡-
  • ኮካ ኮላ ፋብሪካ፣
  • ሌክሾር ሪዞርት፣
  • ድብ አምበሳ ሆቴል፣
  • ግራንድ ሆቴል፣
  • ብሉ ናይል ሪዞርት ሆቴል፣
  • ኩሪፍቱ ሆቴልና
  • ራህ ናይል ሆቴል
እጣቢ ቆሻሻ ወደ ሃይቁ የሚለቁ ድርጅቶች፡-
  • በርኖስ አርት ጋላሪ፣
  • መንግስቱና ፍሬው የመኪና እጥበትና ጋራጅ
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም