ዜጎች የሚያዋጣቸውን ፓርቲ በመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀረበ

288

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) ምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች በድምጽ መስጫ ቀን ይበጀኛል፣ ያዋጣኛል የሚሉትን ፓርቲ በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀረበ።
ብልጽግና ፓርቲ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በራሪ ወረቀቶችን በአውሮፕላን በመበተን ቅስቀሳ አካሄዷል።
ብልጽግና ፓርቲ "ኑ 6ኛው አገራዊ ምርጫ እንምረጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጃቸውን በራሪ ወረቀቶች ዛሬ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በአውሮፕላን በመበተን ቅስቀሳ አካሄዷል።

በዚህ ወቅትም ዜጎች "ድምጼን እንጂ ህይወቴን ለማንም ፓርቲ አልሰጥም" በሚል ለምርጫው ሰላማዊና ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥር ቀርቧል።

ፓርቲው ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ በአቢሲኒያ የበረራ ትምህርት ቤት አውሮፕላን በመታገዝ በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች የፓርቲውን ሃሳብ የያዙ በራሪ ወረቀቶች አሰራጭቷል።

በተለያዩ ምክንያቶች የፓርቲው ሀሳብ ላልደረሳቸው ሰዎች የፓርቲውን ሀሳብ ተደራሽ ለማድረግ የቅስቀሳ ወረቀቱ እንዲበተን መደረጉ ተመልክቷል።

በራሪ ወረቀቱን በአውሮፕላን ካሰራጩት መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ደራሲ፣ ጋዜጠኛና የማህበረሰብ አንቂ እጩ ዶክተር ዮናስ ዘውዴ እንዳሉት፤ በተበተነው የቅስቀሳ ወረቀት የፓርቲው ዓላማ፣ ግብ፣ ማኒፌስቶና ፖሊሲዎችን ለማንጸባረቅ ተሞክሯል።

የምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች በምርጫው ቀን ድምጻቸውን ለሚፈልጉት ፓርቲ በመስጠትና ሌሎችም እንዲመርጡ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ለምርጫው ሰላማዊና ስኬታማነት የሁሉም ዜጎች አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የጠቆሙት እጩ ዶክተር ዮናስ፣ "መራጮች ድምጼን እንጂ ህይወቴን ለማንም አልሰጥም" በሚል ለምርጫው ሰላማዊነትና ስኬታማነት እንዲንቀሳቀሱም አስገንዝበዋል።

ከምርጫው በኋላም ያሸነፈው ፓርቲ አሸናፊነትን በከፍተኛ ሃላፊነት፤ ተሸናፊውም በጸጋ ለመቀበልና ለቀጣይ ምርጫ ዝግጁ መሆን እንዳለበት ነው የተናገሩት።

የአውሮፕላኑ አብራሪና አቢሲኒያ የበረራ ትምህርት ቤት ዋና ዳይሬክተር ካፒቴን ሰለሞን ግዛው በበኩላቸው ዜጎች የቀጣይ መሪያቸውን ሌላ ሰው እንዳይመርጥላቸው ድምጻቸውን ለሚፈልጉት ፓርቲ በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን መጠቀም እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ጠቅላላ ምርጫው አሁን በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ካለው የእርስ በርስ ጥላቻም ሆነ ፍቅር ጋር ከማያያዝ ይልቅ የኢትዮጵያን የወደፊት እድል የሚወስን የሎተሪ ትኬት አድርጎ ማየት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም