ቀይ መስቀል በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን ለተፈናቀሉና ለችግር ለተጋለጡ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገለጸ

60

አክሱም፣ ሰኔ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን ለተፈናቀሉና ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አሰታወቀ።

በማህበሩ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቴድሮስ ሞላው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማህበሩ በዞኑ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች የሰብአዊና የማህበራዊ አገልገሎት ድጋፎች እያደረገ ነው።

በዞኑ እስካሁን ለ5 ሺህ 600 ተፈናቃይ አባወራዎች የምግብ ማብሰያና የንጽሀና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሁም አልጋና ብርድልብስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል ።

በመጠለያ ጣቢያዎች አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 120 ነፍሰጡር እናቶች በነፍስ ወከፍ የ1 ሺህ ብር ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።

በዞኑ በአስገደት ጸንበላ ወረዳ በእንዳባጉና ከተማ ለችግር ለተጋለጡ 850 ወገኖች 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ማህበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በመድሀኒትና በውሀ አቅርቦት እንዲሁም አካባቢ ንጽህና ጨምሮ በበሽታ መከላከል ስራዎች በመሳተፍ አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ካለው የተፈናቃይ ቁጥር አንጻር እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ጠቁመው ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሀላፊው አስታውቀዋል ።

በሽሬ ከተማ አዲከቲባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል ወይዘሮ ትዕበ አፈወርቄ ማህበሩን የአልጋ፣ ብርድልብስ፣ ምግብ ማብሰያና ሌሎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል ።

በተመሳሳይ መልኩ ማህበሩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዳደረገላቸው የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ስላስ ገብረእግዚአብሄር ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም