በጎንደር ከተማ የተወዳዳሪ ፓርቲ ፖስተር እና ባነር በመቅደድ ጥፋት የተከሰሱ ግለሰቦች ተቀጡ

149

ጎንደር፣ ሰኔ 9/2013 በጎንደር ከተማ የተወዳዳሪ ፓርቲ ፖስተር እና ባነር በመቅደድ ጥፋት የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በገንዘብ መቀጣታቸውን የከተማ አስተዳደሩ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የወንጀል አቃቢ ህግ አቶ ደረሰ ዘለለው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ የቀበሌ 18 ነዋሪ የሆነች ግለሰብ ሰኔ 6/2013 ዓ.ም  የፓርቲ መወዳደሪያ ፖስተር መቅደዷን በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጦባታል፡፡

በዚህ ጥፋት ተከሳ ድርጊቱን መፈጸሟን በማመኗ  የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት የ500 ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፎባታል ብለዋል።

በተጨማሪም ሌላ ግለሰብ  ግንቦት 28/2013 ዓ.ም በከተማዋ ቀበሌ 14 ውስጥ   ባነር  ቀዶ ሲጥል በመያዙ አቃቢ ህግ ክስ እንደመሰረተበት ተናግረዋል።

ግለሰቡ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን በፈጸመው ወንጀል የተመሰረተበትን ክስ ክዶ ቢከራከርም በቀረበበት የሰውና የሰነድ ማስረጃ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛነቱን አረጋግጧል።

ፍርድ ቤቱ ባለፈው አርብ በዋለው ችሎት ግለሰቡ ከዚህ ቀደም የጥፋተኝነት ሪኮርድ የሌለው መሆኑን በቅጣት ማቅለያነት በመያዝ የ2ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደተወሰነበት አቃቢ ህጉ አስታውቀዋል።

ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ በተለይም ወጣቱ ከእንደዚህ ዓይነት የጥፋት ድርጊት ራሱን በማቀብ ለዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አቶ ደረሰ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም