ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

67

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2013(ኢዜአ) ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ።

በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የሕዝብን ድምጽ በማክር የሀገሪቱን ዴሞክራሲ ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ በኩል በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።

አባላቱ እንዳሉት በምርጫው የሚሳተፉ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሕዝብን ውሳኔ አክብረው የሀገሪቷን ሰላም ማረጋገጥ ከሁሉም ሥራቸው በላይ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ መሆን አለበት።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ የምክር ቤት አባላት መካከል ወይዘሮ ራቢያ ኢሳ እንዳሉት፣ ፓርቲዎች የሀገር ሰላምንና የሕዝብ ደሕንነትን ለሚያረጋግጡ ማንኛውም ተግባራት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል።

ሰላምን አረጋግጦ የዴሞክራሲ መገለጫ የሆነ ምርጫ እንዲካሔድ መንግስት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሕዝቡ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገሩት።

"በማንኛውም ሀገር ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት እንዲኖር ምርጫ ማካሔድ ወሳኝና ምትክ የማይገኝለት ጉዳይ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ተፈራ በሬቻ ናቸው።

ምርጫን በሰላማዊ መንገድ ማካሔድና የሕዝብን ድምጽ አክብሮ መንቀሳቀስ አንዱ የስልጣኔ መገለጫ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለስኬታማነቱ መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

"ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተአማኒነትን ያተረፈና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል" ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ሰናይት ደስታ።

ከምርጫ ፉክክሩ በኋላም ሁሉም አካላት ልዩነታቸውን በመተው የሀገር አንድነትንና የኢትዮጵያን አሸናፊነት በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆም ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ለሚፈልገው እጩ ተወዳዳሪ ድምጹን የሚሰጥበት ቀን መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም