የኢትዮጵያን ስልጣኔ በአግባቡ ለመረዳት የግዕዝ ቋንቋን መማርና ማስተማር አስፈላጊ ነው -ትምህርት ቢሮ

86

ባህርዳር፤ ሰኔ 9/2013(ኢዜአ) በጥንታዊ እና መካከለኛው ዘመን የነበረው የኢትዮጵያን ስልጣኔ በአግባቡ ለመረዳት የግዕዝ ቋንቋን መማርና ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የግዕዝ ቋንቋ ትምህርትን በአንደኛ ደረጃ በመደበኛ ትምህርት ለማካተት የሚያስችል የምክክር መድረክ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በጥንታዊና መካከለኛው ዘመን የሀገሪቱ አስተዳደር፣ ፍልስፍና፣ ማዕድናት፣ የስነ ፈለግና ስነ ህዋ ስልጣኔ ተሰንደው የሚገኙት በግዕዝ ቋንቋ ነው።

በርካታ የውጭ ሀገራት በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ የህንጻ፣ የመድሃኒት ቅመማ፣ የፍልስፍናና ሌሎች መጻህፍቶችን በመውሰድ ለእድገት መጠቀማቸውን አውስተዋል።

ይህን ስልጣኔና ጥበብ በመመርመርና በማጥናት ለኢትዮጵያን ትንሳኤ መረጋገጥ ለማዋል የግእዝ ቋንቋን መማርና ማስተማር ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ለዚህም አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲዎች የግዕዝ ቋንቋ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ መሰጠቱ ወጣቱ ትውልድ ለግዕዝ ቋንቋና ለጥንታዊ ታሪኮች እውቀት ለመገብየት እንደሚበጅ አስረድተዋል።

አውሮፓውያን ከጨለማው ዘመን ለመውጣት ባካሄዱት የተሃድሶ እንቅስቃሴ የጥንቱን የግሪክና ሮማ ስልጣኔ በማጥናት ከዚህ እውቀት መነሳታቸው አሁን ለደረሱበት እድገት እንዳበቃቸው አስታውሰዋል።

የጥንታዊ የሮማና ግሪክ ስልጣኔን ለመመርመርም የላቲን ቋንቋን በመማር በየዘመናቱ የተከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክዋኔዎችን በማጥናት መነሳታቸው መልካም ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል።

እኛም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫን ዳር ለማድረስ የሀገር በቀል እውቀት ምንጭ የሆነውን የግዕዝ ቋንቋ በመደበኛው ትምህርት ተካቶ እንዲሰጥ መታቀዱንና ይህም የሀገሪቱ ዳግም ትንሳኤ ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በቀጣይም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአረብኛ ቋንቋን ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ መምህር ዶክተር ጥበቡ አንተነህ ባቀረቡት ጽሁፍ እንደገለጹት፤ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መጻህፍት በሀገር ውስጥና ውጭ እንደሚገኙ ጥናቶች ያመላክታሉ።

አሁን ላይ የግዕዝ ቋንቋን ለማስተማር ያስፈለገበት ምክንያት በውጭ ተጽዕኖ የጠፋውን የእውቀት ሽግግር እንደገና በማምጣት ያለፈውንና የመጪውን ትውልድ እውቀት ለማስተሳሰር መሆኑን ተናግረዋል።

ከመጪው ዓመት ጀምሮ የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት ለአምስተኛ ክፍል በሙከራ ደረጃ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ለመስጠት የሚያስችል የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ፣ የመምህራን ስልጠናና ሌሎች ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህም በውጭ ሀገራት አማካኝነት እየደረሰብን ያለውን የባህል ወረራ በመመከት በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመፍጠርና ለመገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ትውልዱን የግዕዝ ቋንቋ እንዲማር ማድረግ የኢትጵያን ትንሳኤ ከማረጋገጥ ተለይቶ መታየት የለበትም ያሉት ደግሞ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ተስፋዬ አባተ ናቸው።

ትውልዱን በግእዝ እውቀት የበለጸገ ለማድረግ ከታሰበ ከኬጂ ጀምሮ በማስተማር አሁን የገጠመንን የፊደልና የድምጽ ልዩነት በማወቅ ችግርን ማለፍ እንደሚቻል ተናግረዋል።

አሁን ላይ ተማርን የሚለው ማህበረሰብ ፊደልና ድምጹን ለይቶ ባለማወቁ የጥንት ጽሁፎችን አንብቦ መገንዘብ ካለመቻሉም በላይ ፊደሎችን አዘበራርቆ ለጽሁፍ ስለሚጠቀም በቀጣይ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም ብለዋል።

ለዚህም ከታች ጀምሮ በመደበኛው ትምህርት የግዕዝ ቋንቋን አካቶ ለመስጠት ቢሞከር አሁን የገጠመውን ችግር በመፍታት ያለፈውን፣ የአሁንና ቀጣዩን ትውልድ ማስተሳሰር እንደሚቻል አስረድተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የምክክር መድረክ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም