ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ለ560 አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር እያከፋፈለ ነው

125

ሐረር፤ ሰኔ 09/ 2013 (ኢዜአ) ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው ለሚገኙ 560 አርሶ አደሮች የሰብል እና አትክልት ምርጥ ዘር እያከፋፈለ መሆኑን ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው የምርምርና ስርጸት ቡድን መሪ አቶ ፈይሳ ሁንዴሳ እንደተናገሩት፤ተቋሙ ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያከፋፈለ የሚገኘው 809 ኩንታል የድንች፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ አተር፣ ሽንብራና የአትክልት ዝርያዎች ነው።

ከዩኒቨርሲቲውና ሌሎች የምርምር ተቋማት በምርምር የተገኙት እነዚህ ምርጥ የሰብል አትክልት ዝርያዎች   በሽታ እና የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ በአካባቢው ምርታማነትን ለማሳደግ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ቀርሳ ኮንቦልቻና ሐረማያ ወረዳዎች  43 ኪሎ ግራም የተለያዩ የአትክልት ምርጥ ዘሮችን በማሰራጨት በ72 ሄክታር መሬት ዘሩ እንዲሸፈን መደረጉን አመልክተዋል።

ቀሪው ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ በመከፋፈል ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ በሐረሪ ክልል እና ድሬዳዋ አስተዳደር ለአርሶ አደሩ የሚሰራጩት ምርጥ ዝርያዎች 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው አቶ ፈይሳ ተናግረዋል::

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ለማ በበኩላቸው፤ የግበርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አዳዲስ እውቀቶች፣ አሰራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያወጣቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩና ለሌሎች ተጠቃሚዎች በማሰራጨት ምርትና ምርታማነት እንዲሻሻል እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከምርጥ ዘር አቅርቦት ሌላ ከከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት ምርታማማነታችን እንዲጨምር እገዛ እያደረገልን ነው፤ እኛም ያገኘውን ቴክኖሎጂ ለሌሎች በማካፈል የማስፋፋት ስራ እያከናወን  እንገኛለን ያሉት የሀረማያ ወረዳ አርሶ አደር ዱርሳ ዩስፍ ናቸው::

በሐረማያ ወረዳ የባቲ ገጠር ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ሬድዋን ረሺድ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ  ከአርሶ አደሩ ጋር በቅርበት የምርምር ስራዎችን እያከናወነ የሚያጋጥሙ ለመፍታት እየደገፋቸው መሆኑን ገልጸዋል::

አርሶ አደሩ ከተቋሙ በሚያገኘው ድጋፍ  ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል::

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት በእጽዋት፣ እንስሳት እና በሌሎች ምርምር ሲያካሂድባቸው የነበሩ 47 የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች በድሬዳዋ አስተዳደር፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች 16 ወረዳዎች ለሚገኙ ከ62ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ማሰራጨቱም ተመልክቷል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም