ለናይል ተፋሰስ አገራት የውሃ ሀብቶቻቸውን በትብብር መጠቀም አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው - የደቡብ ሱዳን የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር

53

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8 ቀን 2013 ( ኢዜአ) የናይል ተፋሰስ አገራት የውሃ ሀብቶቻቸውን በትብብር ማልማትና መጠቀም እንደ አማራጭ ሳይሆን እንደ ግዴታ የሚታይ መሆኑን የደቡብ ሱዳን የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ሚስተር ማናዋ ፒተር ጋትኩት ገለጹ።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን፤ ግብጽ የምስራቅ ናይል የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንድትመለስ ጥሪ አቅርበዋል።

33ኛው የምስራቅ ናይል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ ተካሄዷል።

በውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፣ የደቡብ ሱዳኑ የውሃ ሚኒስትር ማናዋ ፒተር ጋትኩት እንዲሁም የሱዳን የውሃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ ተገኝተዋል።

በውይይቱ የናይል ቤዚን ኢንሸቲቭ የቴክኒክ ባለሙያዎች ታድመዋል።

የደቡብ ሱዳን የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ሚስተር ማናዋ ፒተር ጋትኩት ለናይል ተፋሰስ አገራት የውሃ ሀብቶቻቸውን በትብብር ማልማትና መጠቀም አማራጭ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ ገልጸዋል።

የውሃ ሀብትን በጋራ ማልማት ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ እንደሆነና የአገራት መሪዎች በዚህ ረገድ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ደቡብ ሱዳን በሚኒስትሯ በኩል ግብጽ ወደ  የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት እንድትመለስ ጥሪ አቅርበዋል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከ20 ዓመት በላይ በዘለቀው የናይል ቤዚን ኢኒሺዩቴቭ ትብብር አማካኝነት ተጨባጭ የሚባሉ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

የጋራ የውሃ ሀብቶችን አጠቃቀም ላይ የሚሰራውን የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት (ኢንትሮ) መቋቋም ከስኬቶቹ መካከል ይገኝበታል ብለዋል።

በምስራቅ ናይል በሚገኙ አገራት የሚያደርጉት ድጋፍ የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ጽህፈት ቤቱ በውሃ ሀብት እቅድ፣ አስተዳደርና ልማት የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በናይል ተፋሰስ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ቀጠናዊ የፖሊሲ ውይይቶች መደረጋቸውንና ወጣቶችም በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ የውሃ ሃብትን በትብብር መጠቀምን የሚያጎሉ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ እንደቆዩም ነው ያስረዱት።

የተገኙ ስኬቶች ቢኖሩም የናይል ቤዚን የትብብር ማዕቀፎችን ተጠቅሞ የተፋሰሱ አገራት የውሃ ሃብታቸውን በሚፈለገው መጠን በጋራ እያለሙ አይደለም ብለዋል።

የውሃ ሃብትን በጋራ መጠቀም የሚያስችሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች በቂ ፋይናንስ አለመመደብና የቁርጠኝነት ማነስ እንደሚታይ አመልክተዋል።

የናይል ተፋሰስ አገራት የተለያዩ የውሃ ሀብቶቻቸውን መጠቀም የሚችሉበትን አማራጭ በመጠቀም በአገራቱ ለሚገኙ የልማት ፍላጎት ምላሽ መስጠት እንደሚችሉ ነው ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ የገለጹት።

በዚህ ረገድም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች በቀጠናው አገራት መካከል ትብብርና ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም በጋራ ለማደግ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም በቀጠናው ያለውን የሃይል ትስስር ለማጠናከር ግድቡ የሚኖረው አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ግብጽ ራሷን ካገለለችባቸው የምስራቅ ናይል የሚኒስትሮች ምክር ቤትና የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት እንድትመለስ እንዲሁም ኤርትራም ጽህፈት ቤቱን እንድትቀላቀል ኢትዮጵያ ጥሪ እንደምታቀርብ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ ስር በሚገኙ የተለያዩ ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በማጠናከር በውሃ ሀብት ላይ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታት አገራት ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሱዳን የመስኖና ውሃ ሀብት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ፤ የናይል ተፋሰስ አገራት ከ"ሳጥን ውጪ በማሰብ" ዜጎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የውሃ ሀብት ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የተፋሰሱ አገራት የውሃ ሀብታቸውን በጋራ ለመጠቀም የልማት አጋሮችን እርዳታ መጠበቅ እንደሌለባቸውና ለፕሮጀክቶች ከበጀታቸው አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

አገራትም የውሃ ሀብት ልማት ፕሮጀክት ኢንቨስትመንት ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።

የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ ሴክሬተሪያት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሰይፈዲን አብደላ የናይል ተፋሰስ አገራት የውሃ ፖለቲካውን ወደ ጎን በመተው በውሃ ሀብት አጠቃቀም ያሉ አለመግባባቶችን በናይል ቤዚን ማዕቀፍ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ ናይል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀ መንበር ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም