በጋምቤላ ክልል የኦዲት ምርመራ ግኝት ይፋ ተደረገ

68
ጋምቤላ ሀምሌ 27/2010 በጋምቤላ ክልል በመንግስት መስሪያ ቤቶች በተካሄደ የኦዲት ምርመራ ከ349 ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድልት ፣ የሰነድ ክምችትና ያልተገቡ ክፍያዎች ተፈጽሞ መገኘቱን የክልሉ ኦዲተር ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ጀኔራል ዋና ኦዲተር አቶ ጋርዊች ኩን የቢሮውን የእቅድ አፈፃፀም ለክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት በ2010 በጀት ዓመት በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የኦዲት ምርመራ ተደርጓል፡፡ በኦዲት ምርመራው መሰረት በክልሉ 18 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከ5 ሚሊዮን 300ሺህ ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል፡፡ በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ደግሞ 15 ሚሊዮን 700ሺህ ብር ያልተገባ የውሎ አበል፣ ከኮንትራት ውል ውጪ ክፍያና በበጀት ዓመቱ ያልተሰራ መንገድ እንደተሰራ ተደረጎ መከፈሉን በኦዲት ምርመራ ተደርሶበታል፡፡ ስድስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች በውክልና ከሰበሰቡት ገቢ  ከመንግስት ፋይናንስ መመሪያ ውጪ ለስራ ማስኬጃ አውለው እንደተገኙ አቶ ጋርዊች ገልጸዋል፡፡ በአራት መስሪያ ቤቶች  መመሪያን ያልተከተለ ግዥ ተፈጽሞ ተገኝቷል። ከክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የቀረበውን የሂሳብ ሪፖርት መሰረት በማድረግ በተከናወነው የኦዲት ግኝት መሰረት በጥቅሉ ከ187 ሚሊዮን ብር በላይ በክልሉ በሚገኙ 42 መስሪያ ቤቶች፣ በዞንና በወረዳ በሚገኙ ጽህፈት ቤቶች ያልተወራረደ የሰነድ ክምችት ተገኝቷል። እንዲሁም እስከ ወረዳ በሚገኙ መስሪያ ቤቶች ከ137 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፋይ የሰነድ ክምችት እንዳለም አመልክተዋል። የኦዲት ምርምራ ከተካሄደባችው መስሪያ ቤቶች መካከል የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ፣ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ፣የወጣቶችና ስፖርት፣ የንግድና ኢንዱስተሪ ቢሮዎች፣ ፣የክልሉ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ይገኙበታል። ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ የኦዲት ግኝቶችን መሰረት  የገንዘብ ማስመለስና ከአቅም በላይ የሆኑትንም ጉዳያቸውን በህግ እንዲታይ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም የመንግስትና የህዝብ  ሀብት የፋይናንስ መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ለብክንት እንዳይደርግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው ለስኬቱ የምክር ቤቱ ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ አቶ ጋርዊች ጠቁመዋል። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አታርፋ ሙስጦፋ በሰጡት አስተያየት ዋና ኦዲተር መስረያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ አበረታች ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል። "ከመንግስት ደንብና መመሪያ ውጪ የህዝብና የመንግስት ሀብትን ለብክነት የዳረጉ አካላት በህግ እንዲጠየቁ  ከምክር ቤቱ ትልቅ ስራ ይጠበቃል" ብለዋል። የመንግስት የፋይናንስ ደንብና መመሪያን የሚያስተገብሩ ተቋማት ሳይቀሩ በድርጊቱ እየተሳተፉ መገኘታቻው  የሚያሳዝን ተግባር መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ  አባል አቶ እስማኤል ገለታ ናቸው። "የመንግስት ገንዘብን ከመመሪያ ወጪ ለብክነት የሚደርጉ አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል" ብለዋል። አቶ ኦኬሎ ኡማን የተባሉት የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው በተያዘው የበጀት ዓመት የኦዲት ግኝቶችን በማስመለስ በኩል የምክር ቤቱ አባላት ጠንካራ አቋም ሊይዙ እንደሚገባ አመልክተዋል። የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ሐምሌ 19 እና 20 /2010 ዓ.ም ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ማካሄዱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም