ለመጪው ዓመት ከተያዘው በጀት ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለማኅበራዊና ኢኮኖሚ መስኮች የሚውል ይሆናል

52

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) ለመጪው 2014 በጀት ዓመት ከተደለደለው የመደበኛና ካፒታል በጀት 59 ነጥብ 7 በመቶው ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለጤናና ለከተማ ልማት ዘርፎች መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለፁ።

ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል መንግስት የ2014 ረቂቅ በጀት ላይ ባካሄደው ውይይት ነው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በ2014 በጀት ዓመት ተግባራዊ የሚደረገውን በጀት አስመልክተው ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ለቀጣዩ ዓመት ከተያዘው የመደበኛና የካፒታል በጀት ከግማሽ በላይ የሚሆነው ትኩረቱን በመንገድ፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በውሃ፣ በጤናና በከተማ ልማት መስኮች ማድረጉን ገልጸዋል።

ለመደበኛ ወጪ የተደለደለው 162 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በ2013 ፀድቆ ከነበረው በጀት ጋር ሲነፃፀር የ21 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ እንዳለውና ሁሉን አካታች የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ለካፒታል ወጪ የተመደበው በጀት 183 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር፤ ለክልል መንግስታት የበጀት ድጋፍ ደግሞ 204 ቢሊዮን ብር መሆኑንም አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ ጠቅላላ የፌዴራል መንግስት ገቢ መጠን የውጭ ዕርዳታን ጨምሮ 435 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት የገለጹት ሚኒስትሩ ይህም በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚገኝ ከሚጠበቀው ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ24 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት እንዳለው አክለዋል።

ከዚሁ ገቢም 369 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወይንም 84 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው ከአገር ውስጥ እንደሚገኝ ታሳቢ መደረጉን ጠቁመዋል።

ቀሪው 125 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ከውጭ አገር ብድርና ዕርዳታ የሚገኝ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ 8 ነጥብ 7 በመቶ እንደሚሆን የተተነበየ ሲሆን የዋጋ ግሽበቱም ወደ ነጠላ አሃዝ እንደሚወርድ ይጠበቃል ነው ያሉት ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ።ምክር ቤቱም የቀረበለትን የ561 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የ2014 በጀት ዓመት የመንግስት ረቂቅ በጀት ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም