በጎረቤት አገሮች የችግኝ ተከላን በተመለከተ ለአምባሳደሮች ገለጻ ተሰጠ

49

ሰኔ 8/2013 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በጎረቤት ሀገሮች ችግኝ ለመትከል በተያዘው ዕቅድ ዙሪያ በጎረቤት አገሮች ተቀማጭ ለሆኑ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ አምባሳደሮች በበይነ መረብ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ደመቀ በሀገሪቱ ለ3ኛ ጊዜ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘው የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር የክልል ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማስጀመራቸውን አስታውሰው ፤ በያዝነው ዓመት 1 ቢሊዮን ችግኝ ደግሞ በጎረቤት አገሮች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጎረቤት አገሮች የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ከአገሮቹ ጋር በኢኮኖሚ ፣በሰላም ፣የህዝብ ለህዝብ እና የመንግስታት ግንኙነት ለማጠናከር እና የፓን አፍሪካዊነትን ለማሳየት የአረንጓደ ልማት ትብብር በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን አቶ ደመቀ አስረድተዋል፡፡

በየአገሮቹ የሚተከሉ ችግኞች የአገሮቹን ሥነ ምህዳር እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን በማረጋገጥ ፤እያንዳንዱ ሚስዮን የሚመለከታቸውን መሥሪያ ቤት ጋር ቀርቦ የፍላጎት እና የድርጊት መርሃ ግብር መረጃ አንዲያሳውቅ እንዲሁም ችግኞቹ ከተተከሉ በኃላ ክትትል የሚደረግበት ሥረዓት እንዲዘጋጅ ለአምባሳደሮቹ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

የችግኝ ተከላው ስኬታማ ይሆን ዘንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣የግብርና ሚኒስቴር ፣ የአከባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ፤የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች መሥሪያቤቶች በቅንጅት እንደሚሰሩ አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡

የችግኝ ተከላውም የአገሮቹ ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች ፣በአገራቱ ነዋሪ የሆኑ የዳያስፖራ አባላት እና ሌሎች የሚመለከታቸውን በማሳተፍ በኦፍሰላዊ ሥነ ሥረዓት የሚጀመር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አምባሳደሮች የችግኝ ተከላውን ፋይዳ በመገንዘብ ፤ በየአገሮቹ ከሚመለከታቸው መሥሪያቤቶች ጋር ውይይት በማድረግ ለዕቅዱ ስኬታማነት ወደ ሥራ መግባታቸውን አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም