የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸውን ስቴዲየሞች የመለየት ስራ ሊከናወን ነው

83

ሰኔ 07/2013 (ኢዜአ) የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቀጣይ ዓመት ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸውን ስቴዲየሞች የመለየት ስራ ሊከናወን መሆኑ ተገለጸ ።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎቹ በደቡብ አፍሪካው ዲጂታል ሳተላይት ቴሌቪዥን (DSTV) መተላለፋቸው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት በር ከፋች ነው ብለዋል።

ጨዋታዎቹ በቀጥታ ስርጭት መተላለፋቸው ከውድድሩ ባለፈ በየአካባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ ባህሎችና ቅርሶችን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ለሀገሪቱ ቱሪዝም እደገት ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል።

"ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ" በሚል መጠሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የ2013 ዓ.ም ውድድር ስኬታማ  እንደነበርም ነው ያስታወሱት።

ነገር ግን በቀጣይ ውድድሩን ከዚህ በላይ ለማሳደግ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውንም አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ውድድሩ በአምስት የኢትዮጵያ ከተሞች መከናወኑን አስታውሰው፤ የአንዳንድ ስቴዲየሞች ይዘት የሀገሪቱን ገጽታ የሚያጎድፉ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ዓመት የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታዎች በተሻለ መንገድ ለማካሄድ ብቁ የሆኑ ሜዳዎችን ለመለየት የስታዲየሞቹን ሁኔታ የሚገመግም ኮሚቴ መቋቋሙን ነው የገለጹት።

በቂ የሆነ መለማመጃ ቦታና ደረጃቸውን የጠበቁ ማረፊያ ሆቴሎች መኖራቸውን ማረጋገጥ ከመገመገሚያ መስፍርቶቹ መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።

የከተሞች አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታም ሌላኛው የመገምገሚያ መስፈርት መሆኑን ተናግረዋል።

ለውድድሩ የተመረጡ ስቴዲየሞች የመብራት አገልግሎታቸውን ማስተካከል ከቻሉ ጨዋታዎች ምሽት ላይ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል።

ይህን ማሳካት ከተቻለ የሀገሪቱን የእግር ኳስ ደረጃ በአጭር ጊዜ ማሳደግ ይቻላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ከዲ.ኤስ.ቲቪ ጋር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።

ከተደረገውየቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭትና ስያሜ ሽያጭ በመጀመሪያው ዓመት ለማህበሩ 4 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡

ክፍያው በየዓመቱ በ250 ሺህ ዶላር እየጨመረ እንደሚሄድም ተገልጿል።

በዚህ ዓመት ከዲ.ኤስ.ቲቪ ከተገኘው ገቢ ከአሸናፊው ፋሲል ከተማ አንስቶ ወራጆቹን ክለቦች ጨምሮ እንደ ደረጃቸው በቅደም ተከተል ከ10 ሚሊዮን እስከ 8 ሚሊዮን ብር አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም