ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብርና የቻይናው አሊባባ ኩባንያ በኢትዮጰያ የፋይናንስ ዘርፎች ሊሰማሩ ነው

63
አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2010 ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብርና የቻይናው አሊባባ አጋር 'አንትስ' ተቋም በኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ መስራት እንደሚፈልጉ ገለጹ። ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የዓለም አቀፉን የፋይናንስ ትብብር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የቻይናው አሊባባ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚን ዛሬ በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል። በዚሁ ወቅት የተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ ለፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ገልፀውላቸዋል። ተቋማቱ  በአፍሪካ የሞባይል ስልኮችን በመጠቀም የፋይናንስ እንቅሰቃሴ አገልግሎቶችን ማቅረብ የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርፀው መስራት ይፈልጋሉ። ለአፍሪካ ህዝቦች ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ይኖሩታል የተባለው ፕሮጀክቱ በወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና ሌሎች ምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ አትኩሮ የሚሰራ መሆኑም ተገልጿል። ተቋማቱ የፕሮጀከቱን የመጀመሪያ መዳረሻ ኢትዮጵያ አንድትሆን መምረጣቸውም ተመልክቷል። ከተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ገለፃ የተደረገላቸው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በተለይ በአነስተኛ ገቢ በሚተዳደሩ ዜጎችን ላይ አትኩሮ ከሰራ መንግስት ይደግፋል ማለታቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልፀዋል። የዓለም አቀፉን የፋይናንስ ትብብር ምክትል ፕሬዝዳንት ሚስተር ጂንግ ዶንግ ሁሃ በበኩላቸው፤ የሚመሩት ተቋም ከኢትዮጵያ ጋር የመስራት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል። ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር የዓለም ባንክ አንዱ አካል ሲሆን በግሉ ዘርፍ መዋለ ንዋዩን በማፍሰስ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ይንቀሳቀሳል። ድርጅቱ በአሁን ጊዜ በታዳጊ አገራት 260 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ አቅም አለው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም