በኮቪድ-19 ላይ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው- አቶ ደመቀ መኮንን

69

ሰኔ 5 ቀን 2013 ( ኢዜአ ) በኮቪድ-19 ላይ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎች አሁንም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አገር አቀፍ የኮቪድ-19 የምርምር ጉባኤ "ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ንቅናቄ" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በጉባኤው ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ወረርሽኙን በተመለከተ የሰሯቸው አምስት ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ አቶ ደመቀ መኮንን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከል ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

በኮቪድ-19 ዙሪያ እስካሁን ከተሠራው ይልቅ ያልተሠራው ስለሚበልጥ አሁንም የምርምር ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ወረርሽኙን በተመለከተ እስካሁን ከሚታወቀው በላይ የማይታወቀው ነገር ስለሚበዛ አገራዊ የምርምር አቅም ማሳደግ ተገቢ ነውም ብለዋል።


በዘመቻ መልክ በሚሠራ ሥራ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማግኘት እንደማይቻል የጠቆሙት አቶ ደመቀ ቋሚ የመከላከል ሥራ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ለዚህ ደግሞ የላብራቶሪ አቅም ከማሳደግ ጀምሮ ክትባቱን በስፋት ለመስጠት መዘጋጀት ያስፈልጋልም ብለዋል።

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች ውስጥ ብትሆንም ብርታት፣ ትብብርና አንድነት ካለ ሁሉም ፈተና ይታለፋል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዲሁ ሚኒስቴሩ በኮቪድ-19 ዙሪያ ለተደረጉ የምርምር ሥራዎች 50 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥም አዳዲስ ተመራማሪዎችን መፍጠር የተቻለ ሲሆን ወረርሽኙን መከላከል የሚያስችሉ ውጤቶች ተገኝቷል ነው ያሉት።

በምርምር ሥራዎቹ ከግል ራስ መጠበቂያ ቁሳቁሶች ምርት እስከ የሰውነታችንን የአተነፋፈስ ሥርዓት ተክቶ የሚሠራ ቬንቲሌተር ማሽን ማምረት ድረስ እንደተካሄደ ገልጸዋል።

በቀጣይም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በቅርበት ቢሰሩ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላልም ብለዋል።

በምርምር ሥራዎች የተለዩ ጉዳዮች በግብዓትነት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በቀጣይም ምን ሊመጣ እንደሚችል ስለማይታወቅ መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በለይቶ ማቆያነት፣ በምርምር ማዕከልነትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የሚሰጥባቸው ቦታዎች ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል የሚሉት ደግሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ናቸው።

ከሁሉም በላይ እነዚህ ተቋማት የእውቀት ማመንጨት ሥራ ላይ አተኩረው የመማር ማስተማር ሥራውም እንዳይስተጓጎል ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ነው ያሉት።

በትናንትናው ዕለት የቀረቡ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ጥቅል ሪፖርት ያቀረቡት የአዲስ ኮንቲኔንታል ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ኃላፊ ፕሮፌሰር የማነ ብርሃነ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ይመሰክራሉ።

የተሰሩት የጥናት ሥራዎች ከማከም እስከ ምርመራ ድረስ እንዲሁም ሻል ያሉ ላብራቶሪዎች እስከ ማዘጋጀት የደረሰ ነውም ብለዋል።

ከሁሉም በላይ የተሰሩት ጥናቶች ወጪያቸው የተሸፈነው በመንግሥት በመሆኑ ተመራማሪዎች እንዳይንገላቱም የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹና የምርምር ተቋማቱ ወረርሽኙ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ አንስቶ 150 ገደማ የጥናትና ምርምር ሥራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ወቅት የምርምር ሥራዎችን ላከናወኑ ተቋማት እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን የምርምር ሥራቸውንም በአውደ-ርዕይ መልክ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም